የአምስት አጎራባች ክልሎች ፖሊሶች ተቀናጅተው ያደረጉት የወንጀል መከላከል እንቅስቃሴ ውጤታማ ነው ተባለ

አዳማ ሚያዝያ 9 /1998 ዋኢማ/ በምሥራቅ ኢትዮጵያ ሊፈጸሙ የሚችሉ ወንጀሎችን አስቀድሞ ለመከላከል የአምስት አጎራባች ክልሎች ፖሊስ ኮሚሽኖች በጋራ ተቀናጅተው ያደረጉት የወንጀል መከላከል እንቅስቃሴ ውጤታማ መሆኑ ተገለፀ።

የፖሊስ ኮሚሽኖቹ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተከናወኑትን የወንጀል መከላከል ሥራዎች ትናንት በአዳማ ከተማ በጋራ በገመገሙበት ወቅት እንዳስታወቁት፤ ወንጀልን ለመከላከል በአምስቱ አጎራባች ክልሎች መካከል የነበረው የመረጃ ልውውጥ ፈጣንና ወቅታዊ በመሆኑ ቀደም ሲል ይፈጸሙ የነበሩ የተለያዩ ወንጀሎች እየቀነሱ መጥተዋል።

በምሥራቅ ኢትዮጵያ የተቋቋመው የአምስቱ አጎራባች ክልሎች ጥምር የጋራ የወንጀል መከላከል ኮሚቴ ከአንዱ ክልል ወደ ሌላ ክልል ተዘዋውረው ወንጀልን በመፈጸም የሕብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት የሚያደፈርሱት ፀሬ ሰላም ሀይሎችን አሳልፈው በመስጠት ረገድ የተሳካ እንደነበር አስረድተዋል።

እንደዚሁም ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ዝውውርን ለመግታት በጋራ ባደረጉት የሥራ እንቅሰቃሴ ዙሪያ የታዩትን ጠንካራና ደካማ ጎኖች ላይ ሰፊ ውይይት ካደረጉ በኋላ በቀጣይነት ይበልጥ ለመሥራት ተሰማምተዋል።

ከአምስቱ አጎራባች ክልሎች በተጨማሪ በደቡብ ኢትዮጵያ ቦረና ዞን በኩል የተቋቋመው ሌላው የጋራ ጥምር ኮሚቴም በድንበር በኩል ከኬንያ ፖሊስ ጋር ተገናኝተው ወንጀልን ለመከላከል በጋራ ያደረጉት የሥራ እንቅስቃሴ ውጤታማ እንደነበረ ኮሚሽነሮቹ ተናግረዋል።

በአንዳንድ አከባቢዎች ይነሱ የነበሩ ግጭቶችን በውይይት ለመፍታት፣ ጥፋተኞችን ለፍርድ በማቅረብ እንዲሁም የተዘረፉ ንብረቶችን በማስመለስ በኩል የተደረጉት እንቅስቃሴዎች አበረታች መሆናቸውን ተሰብሳቢዎቹ ገልጸዋል።

ይህ ውጤታማ የወንጀል መከላከል እንቅስቃሴ ሊገኝ የቻለው ጥምር ኮሚቴው እስከ ቀበሌ ድረስ በመውረድ የቀበሌ ታጣቂዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች እንዲሳተፉ በማድረጉ ለወንጀሉ መቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስታውቀዋል።

በዚሁ የሥራ ግምገማ ላይ በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የክልሎች ማስተባበሪያ ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ተስፋዬ አብርሃን ጨምሮ ከኦሮሚያ፣ሐረሪ፣ሱማሌ፣አፋርና ከድረዴዋ የተወጣጡ ፖሊስ ኮሚሽነሮች፣የየዞኑና ወረዳ ፖሊስ ኃላፊዎች ጨምሮ ከ50 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ተሳታፊ መሆናቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።