|
በክልሉ ከ26 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የ77 ኪሎሜትር የመንገድ ስራና ጥገና እየተከናወነ ነው |
| ሐረር ጥር 26/1998/ዋኢማ/ በሐረሪ ህዝብ ክልል ዘንድሮ ከ 26 ሚሊየን ብር በሚበልጥ ወጪ የ77 ኪሎ ሜትር አዲስ የአስፋልት መንገድ ሥራና የነባር መንገዶች ጥገና በመከናወን ላይ መሆኑን የክልሉ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ኃላፊ ኢንጂነር ሳላሃዲን መሐመድ ዛሬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ የአስፋልትና የጠጠር መንገድ ሥራና ጥገናው ካለፈው ወር ጀምሮ በመካሔድ ላይ የሚገኘው በሐረር ከተማና በክልሉ 17 የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ ነው።
በሀገር ውስጥ ተቋራጮችና በጽህፈት ቤቱ ባለሙያዎች በመከናወን ላይ ከሚገኙት የመንገድ ስራዎች መካከል የ5 ኪሎ ሜትር አዲስ የአስፋልት መንገዶች ግንባታ እንደሚገኝበት ኃላፊው ጠቁመው በሐረር ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የ6 ኪሎ ሜትር ነባር የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ጥገናም ከሚሰሩት ውስጥ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ እንዲሁም የክልሉን 17 የገጠር ቀበሌዎች ከሐረር ከተማ ጋር የሚያገናኙ 15 ዋና ዋና መስመሮች ላይ የ66 ኪሎ ሜትር ጠጠርና ጥርጊያ መንገዶች ሥራና ጥገና በመከናወን ላይ ላይ መሆኑን ኢንጂነር ሳላሀዲን አመልክተዋል። በተለይም በኤረር ወልዲያ ገጠር ቀበሌ ገበሬ ማህበር የሚገኘው የኡላን ኡላ -ኮራ 3 ኪሎ ሜትር የገጠር መንገድ ሙሉ በሙሉ በመበላሸቱ ባለስልጣኑ አዲስ ተለዋጭ መንገድ በመሰራት ላይ መሆኑን አስረድተዋል። በገጠር ቀበሌዎች የሚካሔዱት የመንገድ ስራዎች ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁም የየቀበሌዎቹ አርሶአደሮች ምርታቸውን ለገበያ ለማቅረብ የነበረባቸው ከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር እንደሚቃለል ኃላፊው አመልክተዋል። ለመንገዶቹ ግንባታ ከተመደበው 26 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ውስጥ 17 ሚሊየን ብር በክልሉ መንግስት የካፒታል በጀት የተሸፈነ ሲሆን ቀሪው ከመንገድ ፈንድ የተገኘ መሆኑን ከኃላፊው ገለጻ ለመረዳት ተችላል። |
|
|
|
|