|
በሐረር ከተማ በየደረጃው የሚገኙ መምህራን ተካፋይ የሚሆኑበት ሀገር አቀፍ ኮንፍረንስ ሊካሔድ ነው |
ሐረር ጥር 26/1998/ዋኢማ/ በሐረሪ ህዝብ ክልል ከመጪው እሁድ ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ መምህራን ተካፋይ የሚሆኑበት ሐገር አቀፍ የመምህራን ኮንፍረንስ በሐረር ከተማ እንደሚካሔድ የክልሉ ትምህርትና አቅም ግንባታ ቢሮ አስታወቀ። የኮንፍረንሱ ዓላማ በሐገር አቀፍ ደረጃ በወጡ የመንግስት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይ በመወያየት የጋራ ግንዛቤ መያዝና በሀገሪቱ በመተግበር ላይ ያለውን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ማጎልበት እንደሆነ የቢሮው ኃላፊ አቶ ነቢል ማህዲ ገልጸዋል። እንዲሁም የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅና የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ ለማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታና በትምህርት እቅድ አፈጻጸም ያጋጠሙ ችግሮችን ለመገምገምና ከመምህራኑ ጋር ለመወያየት መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል። መምህራኑ ውይይት ከሚያደርጉባቸው የውይይት አጀንዳዎች መካከልም ዴሞክራሲና ዴሞክራሲያዊ ሂደት በኢትዮጵያ፣ የግብርናና ገጠር ልማት ስትራቴጂ እንዲሁም የመምህራን ግንኙነት በትምህርት ተሳትፎ የሚሉ ርዕሶች ይገኙበታል።
ከጥር 28 እስከ የካቲት 11/1998 በሚካሔደው በዚሁ ውይይት ወደ 2000 የሚጠጉ የክልሉ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ተካፋይ እንደሚሆኑና 4 የውይይት መድረኮች እንደተዘጋጁ ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም በተካሔዱት ሀገር አቀፍ የመምህራን ኮንፍረንሶች በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ መምህራን በመንግስት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይ ባደረጉት ውይይት ጠቃሚ ውጤቶች መመዝገባቸውንም አቶ ነቢል አስረድተዋል። |
|
|
|
|