|
በሐረሪ
ህዝብ ክልል 62 ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል ላላቸው ባለሃብቶች ፈቃድ ተሰጠ |
| ሐረር ታህሳስ 25/1998 /ዋኢማ/ በሐረሪ ህዝብ ክልል
ባለፉት 6 ወራት ከ 62 ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል ላላቸው 46 ባለሀብቶች ፍቃድ መስጠቱን የክልሉ ኢንቨስትመንት ጽሀፈት ቤት
አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ መፍቱ ሸሪፍ ዛሬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት ጽህፈት ቤቱ እስከ ትናንት ድረስ ፈቃዱን የሰጠው በክልሉ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሰማራት ጥያቄ ላቀረቡ የሀገር ውስጥ ባለሐብቶች ነው። በኢንዱስትሪ፣ በሪልስቴት፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣በሆቴልና በኮንስትራክሽን ዘርፎች ለመሰማራት ፈቃድ የተሰጣቸው እነዚሁ ባለሀብቶች ሥራ ሲጀምሩ ለ758 ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል እንደሚፈጥሩ ሀላፊው ተናግረዋል።
በተለይም በኢንዱስትሪ ዘርፍ ፈቃድ የተሰጣቸው ባለሀብቶች ከሚሰማሩባቸው የሥራ መስኮች መካከል የሳሙና ፣ የፕላስቲክና ጫማ ማምረቻ ፣የከረሜላና ዱቄት ፋብሪካዎች እንዲሁም የሲሚንቶ ውጤቶች ማምረቻና የአጥንት ህክምና መስጫ ማዕከል እንደሚገኙበት አስረድተዋል።
እንዲሁም የምግብ ማደራጃ፣የምርት ውጤቶች ማከፋፈያ፣ የዶሮ፣ የወተት ከብት እርባታና ማደለቢያ፣የእንጨትና ብረታ ብረትስራ ፣ ጋራዥ፣ ሆቴልና መዝናኛ፣ ክሊኒክ፣ የቢሮና የመኖሪያ ህንጻዎች ግንባታ ባለሀብቶቹ ከሚሰማሩባቸው ውስጥ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ጽህፈት ቤቱ የአገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል ቀልጣፋ አሰራር በማስፈኑ በተጠቀሰው ጊዜ ፈቃድ የተሰጣቸው ባለሐብቶች ቁጥር ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ቁጥሩ መጨመሩን ሃላፊው አስረድተዋል።
በሌላ በኩልም በሐረር ከተማ በ7ሚሊየን 848 ሺ 400 ብር ወጪ በትውልድ ኢትዮጵያዊ በሆኑ አንድ የውጭ ባለሀብት የተገነባ ዘመናዊ ሆቴልና መዝናኛ ማዕከል ተጠናቆ ለአገልግሎት መዘጋጀቱን ሃላፊው ተናግረዋል።
ዶክተር አብዱልጀዋድ አዱስ በተባሉ ባለሀብት በከተማው ቀበሌ 14 የተገነባው ይሄው ሆቴል የሐረር ከተማን ባህልና ቅርስ በሚያንጸባርቅ መልኩ የተገነባ ሲሆን ለ45 ሰዎች የሥራ እድል እንደሚያስገኝ አስረድተዋል።
የክልሉ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት የዘንድሮውን ሳይጨምር ባለፉት 10 ዓመታት ለ 5 ሺ 668 ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል ላስገኙ ከ200 የሚበልጡ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ፈቃድ መስጠቱንም ከአቶ መፍቱ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል። |
|
|
|
|