የስልጤና የሐረሪ ብሔረሰቦች ልማታቸውን ለማፋጠን የሚያስችለላቸው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መሰረቱ

ወራቤ ጥር 4/1998/ዋኢማ/ የስልጤና የሐረሪ ብሔረሰቦች ለዘመናት ተጭኗቸው ከነበረው ብሔራዊ ጭቆና ተላቀው የጋራ እሴቶቻቸውን ለማበልፀግና ልማታቸውን ለማፋጠን የሚያስችላቸውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ትውውቅ መድረክ መፍጠራቸው ተገለጸ፡፡

ለሁለት ቀናት በወራቤ ከተማ በተካሄደው የስልጤና የሀረሪ ህዝቦች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ትውውቅ መድረክ ላይ የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳኒ ረዲ እንደገለፁት፤ መድረኩ የስልጤና የሀረሪ ብሔረሰቦች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አንድነታቸውን አጠናክረው ድህነትን፣ ኋላቀርነትንና መሀይምነትን ለመታገል የሚያስችላቸው ነው፡፡

የስልጤ ብሔረሰብ ባለፉት መንግስታት የብሔራዊ ጭቆና ሰለባ ሆኖ በመቆየቱ ህዝቡ ቋንቋውን፣ ባህልና ታሪኩን መጠበቅና ማሳደግ ሳይችል ለከፍተኛ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችና ተዳርጎ መቆየቱን አቶ ሳኒ ጠቁመው፤ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ጨቋኝ ስርዓቶች ዳግም እንዳይመለሱ በጋራ ለመታገል እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

የሐረሪ ክልል ህዝብ አደረጃጀትና ባህል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዜይዳን በክሪ በበኩላቸው በታሪክ፣ በባህልና በቋንቋ ተመሳሳይነት ያላቸው የስልጤና የሐረሪ ብሔረሰቦች በነበሩት ጨቋኝ ስርዓቶች አማካይነት የመቀራረብ ዕድል ሳያገኙ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ የትውውቅ መድረኩ መፈጠር ሁለቱ ብሔረሰቦች ትስስራቸውን አዳብረው በልማቱም በኩል በጋራ ለመስራት ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡

በትውውቅ ፕሮግራሙ በስልጤ ዞኑ የሚገኙ ታሪካዊና የቱሪስት መስህብነት ያላቸው ቦታዎች የተጎበኙ ሲሆን፤ የሀረሪ ተወላጅ ባለሐብቶች በስልጤ የልማት እንቅስቃሴ እንደሚሳተፉና በውጭና በሀገር ውስጥ የሚኖሩ ምሁራኖቻቸውም በዕውቀታቸው ልማቱን እንደሚያግዙ አቶ ዜይዳን ጠቁመዋል፡፡

በዞኑና በተለያዩ ከተሞች የሚገኙ የስልጤ ብሔረሰብ ተወላጅ ባለሀብቶች በበኩላቸው በዞኑ በሚገኙ የኢንቨስትመንት አማራጮች መዋዕለ ንዋያቸውን እንደሚያፈሱና የሁለቱን ብሔረሰቦች ግንኙነት ለማጠናከር በሐረሪ ክልልም በሚደረጉ የልማት እንቅስቃሴዎች እንደሚሣተፉ አስታውቀዋል፡፡

የብሔረሰቦቹ የብሔረሰቦቹ ዕምቅ ሀብትና የሰው ኃይልን በመጠቀም በብሔረሰቦቹ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ ስራዎችን ለማከናወን የስምምነት ውል መፈራረማቸውን የደቡብ መገናኛ ብዙኃንን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡