|
የሴቶች ልማት እንቅስቃሴ ፕሮጀክት ለችግረኛ ሴቶች ከ1 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ |
ሀረር ጥር 8/1998/ዋኢማ/ የሐረሪ ህዝብ ክልል የሴቶች ልማት እንቅስቃሴ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ዩኒት በቡድን ለተደራጁ ችግረኛ ሴቶች ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ገለፀ። የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ሙኒር አብዱል ሀሚድ ትናንት ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት ማስተባበሪያው ድጋፉን ያደረገው በሐረር ከተማና በክልሉ የገጠር ቀበሌዎች በ20 ቡድኖች ለተቋቋሙና ከ518 የሚበልጡ አባላት ላሏቸው ችግረኛ ሴቶች ነው። ማስተባበሪያው ቡድኖቹ ያቀረቡትን ፕሮጀክት ከገመገመና ስለገንዘቡ አጠቃቀም ትምህርት ከሰጠ በኋላ እስካሁን ከ1ሚሊየን 33 ሺ 793 ብር በላይ ድጋፍ በማድረግ እንዲቋቋሙ ማድረጉን አስተባባሪው ተናግረዋል። ድጋፉን ያገኙት ሴቶች በሸቀጣ ሸቀጥ፣ በእህልና ጥራጥሬ ፣በከብት መኖ አቅርቦት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በሥጋና ሥጋ ውጤቶች፣ በምግብ ዝግጅት፣ በቆዳ ውጤቶች፣ በጸጉር ሥራ፣ በሆቴልና በሌሎችም አዋጭነት ባላቸው የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ተሰማርተው ራሳቸውን ለመቻል ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ማስተባበሪያው ከገንዘብ ድጋፉ በተጨማሪ በኤች አይ ቪ ኤድስ ፣ በቤተሰብ ምጣኔ፣ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በንቃተ ህግ፣ በሥርዓተ ጾታና ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትና ሥልጠና እንደሚሰጥ አቶ ሙኒር አመልክተዋል። በቡድን ከተደራጁት ሴቶች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም ምንም የገቢ ምንጭ ስላልነበራቸው ችግረኛ ሆነው መቆየታቸውን ጠቁመው ከማስተባበሪያው ድጋፍ ከተደረገላቸው ወዲህ ራሳቸውን ለመቻል ጠንክረው በመስራት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የሐረሪ ህዝብ ክልል የሴቶች ልማት እንቅስቃሴ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ዩኒት በ1995 ተቋቁሞ ለችግረኛ ሴቶች ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሆነ ከአስተባባሪው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል። |
|
|
|
|