|
በሐረሪ
ክልል የሁለት ሺ አርሶ አደሮችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያስቸል እንቅስቃሴ ተጀመረ |
|
ሐረር ጥር 9/1998/ዋኢማ/ በሐረሪ ህዝብ ክልል ከፍተኛ የምግብ እህል እጥረት ባለባቸው የገጠር ቀበሌዎች ሁለት ሺህ የሚጠጉ አርሶ አደሮችን በመደበኛ የኤክስቴንሽን መርሀ ግብር ለማሳተፍ ዝግጅት መጀመሩን የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ።
በቢሮው የግብርና ኤክስቴንሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ ነስረዲን ወራቅ ዛሬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት መርሀ ግብሩ ከተያዘው ወር ጀምሮ የሚካሔደው በክልሉ ከፍተኛ የምግብ እህል እጥረት ጎልቶ በሚታይባቸው አሥር ቆላማ የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ ነው።
በመርሀ ግብሩ 1ሺ 620 አባዎራዎችና180 እማዋራዎች በጓሮ አትክልትና በሰብል ልማት፣ በእንስሳት እርባታ፣ በድህረ ምርት ቴክኖሎጂና በአፈርና ውሀ ጥበቃ ሥራዎች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።
በኤክስቴንሽን ፓኬጅ ታቅፈው እንቅስቃሴ የሚያደርጉት እነዚሁ አርሶ አደሮች በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ሰብሎችን በማምረት የምግብ እህል ችግራቸውን እንደሚያቃልሉ ሀላፊው አስረድተዋል።
በምርት ዘመኑ በሚካሔደው በዚሁ ፕሮግራም ለሚሳተፉ አርሶአደሮች ለማዳበሪያ፣ ለምርጥ ዘር፣ ለውሀ ሞተር መግዣ፣እንዲሁም ለአርሶአደሮችና ለባለሙያዎች ስልጠና 897 ሺ 961 ብር በጀት መመደቡንም ጠቁመዋል።
መርሀ ግብሩ በሁሉም ቀበሌዎች ተግባራዊ ሲሆን 1ሺ800 አርሶአደሮችና ቤተሰቦቻቸው ምርታቸውን ከፍ በማድረግና በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በማምረት በአጭር ጊዜ የምግብ ዋስትና ችግራቸውን ይፈታሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።
በተለይም በልዩ ልዩ የጓሮ አትክልት ፓኬጆች የሚሳተፉ አርሶ አደሮች ምርታቸውን በማሳደግ በአጠቃላይ ከ2ሺ441 ብር በታች የነበረውን አመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢያቸውን ወደ 4ሺ482 ብር ከፍ ለማድረግ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
በሐረሪ ህዝብ ክልል በሚገኙ 17 የገጠር ቀበሌዎች ከ14ሺ200 የሚበልጡ አባወራ አርሶአደሮች እንደሚገኙ ከአቶ ነስረዲን ገለጻ ለመረዳት ተችሏል። |
|
|
|
|