በሐረር ከተማ የቱሪዝም ገቢን ለማሳደግ የሚያስችል ጊዜያዊ የመማክርት ጉባኤ ተቋቋመ

ሐረር ግንቦት 25 /1998 ዋኢማ/በሐረር ከተማ ከቱሪስት መስህቦች የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግና ባለሀብቶች በቱሪዝም ልማት በስፋት እንዲሳተፉና የሚያስችል የቱሪዝም ጊዜያዊ የመማክርት ጉባኤ ተቋቋመ።

የሐረሪ ህዝብ ክልል ንግድ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ የንግድ ኢንዱስትሪና ቱሪዝም ዘርፍ ሀላፊ አቶ ፉአድ አብደላ የመማክርት ጉባኤውን ለማቋቋም ትናንት በሐረር ከተማ በተካሔደው የግማሽ ቀን አውደ ጥናት ላይ እንደገለጹት የመማክርት ጉባኤውን ማቋቋም ያስፈለገው በክልሉ የቱሪስት መስህቦችን የሚጎበኙ የውጭ ሀገር ቱሪስቶችን ቁጥር በመጨመር ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ነው።

የመማክርት ጉባኤው የክልሉን እምቅ የቱሪስት ሀብት ለውጭ ሀገር ቱሪስቶች ለማስተዋወቅ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር የጠቆሙት ሀላፊው በሆቴል፣በትራንስፖርትና በሌሎች የቱሪስት አገልግሎት ዘርፎች የሚታየውን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል እንደሚረዳ ገልጸዋል።

የመማክርት ጉባኤው መቋቋም ባለሀብቶች በቱሪዝም ኢንቨስትመንት በስፋት ተሰማርተው ከመስኩ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ እንደሚያመቻች ጠቁመው፣ በቱሪስት አስጎብኚ ድርጅቶችና ግለሰቦች አማካይነት ከዚህ ቀደም ይታዩ የነበሩ ችግሮችን እንደሚያስወግድ ተናግረዋል።

ከዚህም ሌላ የመማክርት ጉባኤው ሥራ አጥ ወጣቶችና ሴቶች በልዩልዩ የእደጥበብና ጌጣጌጥ ሥራዎች በማሰማራት ምርቶቻቸውን ለውጭ ሀገር ቱሪስቶችና ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ እንደሚፈጥር አስረድተዋል።

ጊዜያዊ የመማክርት ጉባኤው ባለሀብቶችን ጨምሮ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ 18 መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በአባልነት ያካተተ ሲሆን የቱሪዝም ጊዜያዊ መማክርት ጉባኤ ማቋቋሚያ ደንብ በማጽደቅና በክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ከተማ ልማት ቢሮ ሀላፊ በአቶ አብዱራህማን መሀመድ የሚመራ 7 የመማክርት ጉባኤ አመራሮችን መርጧል።

የጊዜያዊ መማክርት ጉባኤው ሲቋቋም ከክልሉ የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች፣ ከሀይማኖት አባቶች ከወጣቶችና ሴቶች ማህበራት፣ ከእድሮች፣ከግል ሙዚየም ባለቤቶች፣ከሆቴሎችና መዝናኛ ቤቶች፣ከትራንስፖርት ድርጅቶችና ፣ ከአስጎብኚዎች እንዲሁም ከተለያዩ ተቋማት የተወከሉ ከ50 የሚበልጡ ተሳታፊዎች መገኘታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜኝን ማዕከል ዘግቧል።