የሐረሪ እና የስልጤ ብሔረሰቦች የህዝብ ለህዝብ ግንኙኑነት የጋራ መድረክ መስራች ጉባኤ ተካሄደ

አዲስ አበባ ሰኔ 4/1998/ዋኢማ/ የሐረሪ እና የስልጤ ብሔረሰቦች የህዝብ ለህዝብ ግንኙኑነት የጋራ መድረክ መስራች ጉባኤ ዛሬ በኦሮሚያ ምክር ቤት አዳራሽ ተካሄደ፤ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ በብሔረሰቦቹ ያለውን የቆየ የታሪክ፣ የባህልና የቋንቋ ትስስር በማጠናከር ድህነትን ለማስወገድና ለዲሞክራሲ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተገልጿል።

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መድረኩን በክብር እንግድነት የከፈቱት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ክቡር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ባደረጉት ንግግር፤ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብትና እኩልነት የተረጋገጠበትን የኢፌዴሪ ህገ መንግስትና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ጠብቆ ለማቆየት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ መስኮች ጠንካራ ትስስር ፈጥሮ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል።

[ድምጽ-የአምባሳደር ተሾመ ቶጋ]

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በእኩልነት፣ በመፈቃቀድና በመፈቃቀር ላይ የተመሰረተ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ለመገንባት በር በከፈተው የግንቦት 20 ድል 15ኛ በዓል በተከበረበት ማግስት በሁለቱም ብሔረሰቦች መካከል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መፈጠሩ ታሪካዊነቱን የላቀ ያደርገዋል ብለዋል።

በሐረሪና ስልጤ ብሔረሰቦች መካከል ዕውን እየሆነ ያለውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ፋይዳው ለሁለቱ ብሔረሰቦች ብቻ አለመሆኑን የገለፁት አፈ ጉባዔው፤ በአገራችን በጋራ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባትን እንዲሁም አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመፍጠር ዓላማን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።

[ድምጽ-የአምባሳደር ተሾመ ቶጋ - ድጋሚ]

የሐረሪ ህዝብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ሙራድ አብዱልሃዲ በበኩላቸው የሐረሪና የስልጤ ብሔረሰቦች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የጋራ መድረክ በብሔረሰቦቹ ያለውን የቆየ የታሪክ፣ የባህልና የቋንቋ ትስስር በማጠናከር ድህነትን ለማስወገድ፣ ለአከባቢ ልማት፣ ለሰላምና ዲሞክራሲ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አስገንዝበዋል።

የሁለቱም ብሔረሰቦች ህዝቦች በመልክዓ ምድር ተራርቀው ቢኖሩም በታሪክ፣ በባህልና በቋንቋ የቆየ ትስስር እንዳላቸው የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ዘውዳዊውና ወታደራዊ የአገዛዝ ስርዓቶች ይከተሉት በነበረው ፖሊሲ ሁለቱ ህዝቦች እንዳይገናኙ ማነቆ ሆኖባቸው መቆየቱን ተናግረዋል።

የሁለቱን ህዝቦች የጋራ እሴቶችን ማበልፀግና ለተተኪ ትውልድ ማስተላለፍ አስፈላጊ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ሙራድ፤ ይህን ማድረግ የሚቻለው ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ጠብቆ ማቆየት ሲቻል እንደሆነ አስገንዘበዋል።

የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ክቡር አቶ ሳኒ ረዲ በበኩላቸው የህዝብ ልጆች ባካሄዱት መራራ ትግልና በከፈሉት መስዋዕትነት በብሔረሰቦቹ ላይ ለዘመናት ተጭኖ የነበረው ብሔራዊ ጭቆና ተወግዶ የብሔር ብሔረሰቦች መብት ህገ መንግስታዊ ዋስትና ማግኘቱን ተናግረዋል።

የስልጤ ህዝብ በ1993 ባካሄደው ህዝበ ውሳኔ ራሱን ችሎ በዞን ደረጃ መተዳደር መጀመሩን የጠቆሙት ዋና አስተዳዳሪው፤ በዚህም ህዝቡ ታሪኩን ባህሉንና ቋንቋውን ለማበልፀግና ልማቱን ለማፋጠን የሚችልበት ሁኔታ መፈጠሩን አስረድተዋል።

ከ1 ሺ500 በላይ የብሔረሰቦቹ ተወካዮችና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት በዚሁ የህዝብ ለህዝብ የግንኙነት መድረክ የብሔረሰቦቹን ባህል የሚያንጸባርቁ አልባሳት፣የመመገቢያና የመገልገያ ቁሳቁስና የሙዚቃ መሳሪዎች በተሳታፊዎቹ የተጎበኙ ሲሆን፤ ልዩ ልዩ ባህላዊ ጭፈራዎች መቅረባቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሸን ማዕከል ዘግቧል።

ዋኢማ

ግመ/ይሠ/ሙተ