ኮርፖሬሽኑ 47 ከተሞችን የዘመናዊ ስልክ ተጠቃሚ የሚያደርግ የማስፋፋት ሥራ እያከናወነ ነው

ድሬዳዋ ሰኔ 17/1998/ዋኢማ/ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን በምስራቅ ኢትዮጵያ የሚገኙ 47 ከተሞችን የዘመናዊ ስልክ ተጠቃሚ ለማድረግ ከ250 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የማስፋፋትና የኬብል ዝርጋታ ሥራ እያካሔደ መሆኑን አስታወቀ። 600 የገጠር ቀበሌዎችን የስልክ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረጉንም ገለጸ።

በኮርፖሬሽኑ የምስራቅ ሪጅን ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንድአውክ አበዜ ዛሬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፤ የማስፋፋትና የኬብል ዝርጋታ ሥራው በመካሔድ ላይ ያለው በኦሮሚያ፣ በሶማሌ፣ በሐረሪና በድሬዳዋ አስተዳደር በሚገኙ የገጠር ከተሞች ነው።

በክልሎቹ በሚገኙ የዞን የወረዳና የገጠር ከተሞች ከሚካሄዱት ፕሮጀክቶች መካከል በድሬዳዋ፣ በሐረር፣ በጅጅጋ እና በአሰበ ተፈሪ ቅርንጫፎች የሚገኙ 33 ከተሞችን አዲስ የዲጂታል አውቶማቲክ ስልክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚካሔድ ግንባታ ይገኝበታል።

እንዲሁም በ14 ከተሞች የኬብል ዝርጋታና የማስፋፋት ሥራ፣35 ሺ ደንበኞችን የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል የአዳዲስ መሳሪያዎች ተከላ ሥራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ አቶ ወንድአውክ ገልጸዋል።

ፕሮጀክቶቹ የተጀመሩት በአብዛኛው የስልክ አገልግሎት ባልተዳረሰባቸው የገጠር ከተሞች መሆኑን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ፤በሚቀጥለው ዓመት መጀመሪያ ሲጠናቀቁ የተንቀሳቃሽ ስልክ ቁጥር አሁን ካለው 21ሺወደ 50ሺ፤የመደበኛ ስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ46ሺ ዋደ 50ሺ የሚደርስ ሲሆን የዲጂታል አውቶማቲክ ስልክ ተጠቃሚ ከተሞች ቁጥር ደግሞ ከ50 ወደ 64 ከተሞች ከፍ እንደሚል አስረድተዋል።

ኮርፖሬሽኑ እስከአሁን ባካሔዳቸው የማስፋፋትና የግንባታ ሥራዎች በሪጅኑ የሚገኙ 600 የገጠር ቀበሌ አስተዳደሮችን የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉንና በበርካታ ከተሞችም አዳዲስ የህዝብ ስልኮች ተተክለው ለአገልግሎት እንዲበቁ መደረጉን አስታውቀዋል።

ከዚህም ሌላ የማስተላለፊያ መስመሩ ወደ ኦፕቲካል ፋይበር ተቀይሮ ፈጣን፣ ጥራት ያለውና ብዙ ደንበኞችን ሊያስተናግድ የሚችል የኮሙኒኬሽን ከፍተኛ መስመር በቅርቡ የሙከራ አገልግሎት መጀመሩን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ ጥራት ያለው የኢንተርኔት አገልግሎት እንደሚሰጥም አስረድተዋል።

ኮርፖሬሽኑ በተጠናቀቀው ዓመት ከ50 በሚበልጡ ከተሞች የስልክ መስመር ማሻሻልና ማስፋፋት ሥራ፣ የማዞሪያ ህንጻና የኔትዎርክ መዘርጋትና ጥገና ሥራዎችን ማከናወኑን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።