የሐረር ከተማን የመጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት የውሃ ፕሮጀክት ግንባታ እየተፋጠነ ነው

ሐረር መጋቢት 8/ 1998/ዋኢማ/የሐረር ከተማን የመጠጥ ውሃ ችግር ለዘለቄታው ለመፍታት በ293 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚካሔደው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ በመፋጠን ላይ መሆኑን የሐረር ከተማ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ አስተባባሪ አቶ አህመድ መሀመድ ዛሬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት የፕሮጀክቱ ግንባታ በመካሔድ ላይ የሚገኘው ሲጂሲ በተባለው የቻይና የኮንስትራክሽን ካንፓኒ አማካኝነት ነው።

ከፕሮጀክቱ አራት ሞተር ጣቢያዎች የሞተር ጣቢያ ቁጥር ሁለት የቦታ ጠረጋና የመሠረት ቁፋሮ ሥራ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ የሞተር ጣቢያ ቁጥር ሦስት ለሪዘርቫየርና ለሞተር ጣቢያ የሚሆን የቦታ ጠረጋ ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመልካ ጀብዱ አካባቢ የቧንቧ መስመር ለመዘርጋት የሚያስችል የቁፋሮ ሥራ ተጀምሮ በመከናወን ላይ እንደሆነና በደንገጎ አካባቢ ደግሞ የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ ለመስራት የቦታ መረጣ ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን አቶ አህመድ ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በሐረር ከተማ የቧንቧ መስመር ለመዘርጋት የሚያስችል የቧንቧ መስመር ቁፋሮ ሥራ መጀመሩን ጠቁመው ፣በተለያዩ ምክንያቶች የተጓተተውን የዚህን የፕሮጀክቱን ሥራ ለማካካስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ከኮንስትራክሽን ድርጅቱ ጋር በተደረሰው ስምምነት መሰረት የፕሮጀክቱ ግንባታ በሁለት ቦታ ተከፍሎ እንደሚካሔድ የጠቆሙት አቶ አህመድ በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ሲካሔድ የነበረው የፕሮጀክቱ የቅየሳ ሥራ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁንም ገልጸዋል።

የፕሮጀክቱ የመጀመሪያው ክፍል ከሐረር ሀሰሊሶ 42 ኪሎ ሜትር የቧንቧ መስመር መዘርጋትና አራት የሞተር ጣቢያዎችና የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳዎች ሥራና ሌሎችም ተዛማጅ ሥራዎችን የሚከናወኑበት መሆኑን አስረድተዋል።

ሁለተኛው የፕሮጀክቱ ግንባታ ደግሞ ከደንገጎ እስከ ሐረር ያለው የ30 ኪሎ ሜትር የቧንቧ መስመር መዘርጋት እንዲሁም በደንገጎና በሐረር ከተሞች ባለ2 ሺ እና ባለ4 ሺ ሜትር ኪዩብ የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከሮች፣ በዓለማያና አወዳይ ከተሞች ደግሞ በእያንዳንዳቸው ባለ2 መቶ ሜትር ኪዩብ የውሃ ማከማቻወችን መትከል መሆኑን አስረድተዋል።

ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ የፕሮጀክቱን ሥራ ለማፋጠን የፕሮጀክቱ ሥራ በሚካሔድባቸው ሥፍራዎች የሚፈጠሩ ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት የካሳ ክፍያ እያከናወነ መሆኑንም አስተባባሪው አመልክተዋል።

በድሬ ጃራ አካባቢ ያለው የከርሰ ምድር ውሃ በሐረር፣ በአለማያ፣ በአወዳይ ፣አዴሌ እና ደንገጎ ከተሞች ለሚኖሩ ከ214 ሺ የሚበልጡ ነዋሪዎች ለአስር አመት በሰከንድ 268 ሊትር ውሃ እንደሚሰጠና ከዚያ በኋላ ደግሞ ሁርሶ አካባቢ ተጨማሪ ጉድጓዶችን በመቆፈር ጥቅም ላይ እንዲውል እንደሚደረግ ገልጸዋል።

በአፍሪካ ልማት ባንክ አሰራር የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች ለማሟላትና የተፈቀደውን የብድርና የእርዳታ ገንዘብ ለማግኘት እንዲሁም ለፕሮጀክቱ አማካሪ መሀንዲስና ተቋራጭ ለመቅጠር ጊዜ በመፍጀቱ የፕሮጀክቱ ግንባታ ተጓቶ መቆየቱን አቶ አህመድ ጠቁመው ፤የፕሮጀክቱ ሥራ በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ለአገልግሎት እስኪበቃ የከተማው ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ባለስልጣን ለአጣዳፊ የውሀ ፕሮጀክቶች ቁፋሮ ትኩረት በመስጠት በአለማያ ሀይቅ ዙሪያ ኢፋ ባቴ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተቆፈሩ የውሀ ጉድጓዶች አማካኝነት በሰከንድ 60 ሊትር ውሀ በመሳብ በቧንቧ ውሀ እያቀረበ መሆኑንም አስረድተዋል።