|
በሃረሪ ህዝብ ክልል የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው |
ሐረር ግንቦት 4 /1998/ዋኢማ/ በሐረሪ ህዝብ ክልል የሥርዓተ ጾታን እንቅስቃሴ ለማጠናከርና ሴቶች በፖለቲካ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የሚጫወቱትን ሚና ለማሳደግ የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን የክልሉ ሴቶች ጉዳይ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የጽህፈት ቤቱ ሀላፊ ወይዘሮ ሀፊዛ በድሪ እንደገለጹት የክልሉ ሴቶች ድህነትን ለማስወገድ በሚደረገው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚጫወቱትን ሚና ለማሳደግ የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች በመከናወን ላይ ናቸው። በዚህም መሠረት የክልሉ ሴቶች ውሳኔ ሰጭነትንና የከፍተኛ አመራር ሚናን በማጎልበት ከዚህ በፊት በክልሉ ምክር ቤት ዝቅተኛ የነበረው የሴት ምክር ቤት አባላት ቁጥር ከ3ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ወዲህ ወደ 30 በመቶ ከፍ ማለቱን አስረድተዋል። እንዲሁም የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ በተደረገው ጥረት በክልሉ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ዝቅተኛ የነበረው የሴት ተማሪዎች ተሳትፎ ዘንድሮ ወደ 43 በመቶ መድረሱን ጠቁመው በ2ኛ ደረጃና በክልሉ ሌሎች የትምህርት ተቋማትም የሴት ተማሪዎች ተሳትፎ እድገት እያስመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል። በአሁኑ ጊዜ በክልሉ ለሴቶች ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እስካሁን በጽሀፈት ቤት ደረጃ የሚገኘውን የክልሉን ሴቶች ጉዳይ ወደ ቢሮ ደረጃ ለማሳደግና የሰው ሀይሉንም ለማጠናከር የሚያስችል ረቂቅ ተዘጋጅቶ ለክልሉ ምክር ቤት መላኩን ገልጸዋል። ረቂቁ ጸድቆ ጽህፈት ቤቱ ወደ ቢሮ ደረጃ ሲሸጋገርም በክልሉ በሴቶች ላይ የሚደርሱትን የሀይል ጥቃቶች ለመከላከልና የሥርዓተ ጾታ ችግሮችን ለማስወገድ የሚደረገውን ጥረት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚያስችልም ወይዘሮ ሀፊዛ ተናግረዋል። እንዲሁም በክልሉ በባህላዊ ና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ሳቢያ በሴቶች ላይ የሚደርሱ እንደ ግርዛትና ብልት ትልተላ የመሳሰሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና ተጽእኖዎችን ለመቀነስና ለማስወገድ እንደሚያስችልም አስረድተዋል። ከዚህም ሌላ በመጪዎቹ ዓመታት የክልሉን ሴቶች ሁለገብ እንቅስቃሴአቸውን በማጠናከር ድህነትን ለማስወገድና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ጽህፈት ቤቱ የሥርዓተ ፆታ እቅድ አዘጋጅቶ ሥራ ላይ የማዋል እቅድ እንዳለውም ወይዘሮ ሀፊዛ ጠቁመዋል። |
|
|
|
|