|
በአጎራባች
ክልሎች ኮንትሮባንድን በጋራ ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ውጤት እያስገኘ መሆኑ ተገለጸ |
| ሐረር ግንቦት6/1998/ዋኢማ/ በምስራቅ ኢትዮጵያ የሚገኙ
አምስት አጎራባች ክልሎች የአካባቢያቸውን ጸጥታ በጋራ ለመጠበቅና የተጀመረውን የፀረ ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ለማጠናከር
የጀመሩት ጥረት አበረታች ውጤት እያስገኘ መምጣቱን የሐረሪ ህዝብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ገለጹ።
ኮሚሽነር ሙራድ አብዱላሒ ትናንት ለዋልታ ኢንፎርሜሸን ማዕከል እንደገለጹት፤ ከሱማሌ፣ ሐረሪ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ ክልሎችና ከድሬዳዋ ጊዜያዊ አስተዳደር የሚገኙ የጸጥታ ሀይሎች ከጉሙሩክና ከሌሎች የጸጥታ ሀይሎች ጋር በመቀናጀት ኮንትሮባንድን ለመከላከል በጋራ የጀመሩት እንቅስቀስቃሴ ውጤት በማስገኘቱ ቀደም ሲል ወደ ሐረር ከተማና አካባቢው በብዛት ይገባ የነበረው የኮንትሮባንድ ሸቀጥ እየቀነሰ መጥቷል።
እንዲሁም የአካባቢያቸውን ሰላምና ደህንነት በጋራ በመጠበቅ፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀለኞችን በመቆጣጠር ፣ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች ዝውውርን በቁጥጥር ስር በማዋልና ወንጀልን በመከላከል ዙሪያ ያደረጉት እንቅስቃሴ አበረታች ውጤት አስገኝቷል።
እንዲሁም ከክልል ወደ ክልል በመዘዋወር የአካባቢውን ሰላም የሚያውኩ ጸረ ሰላም ሃይሎችን ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ለመከላከል የተደረገው ጥረት ውጤት እያስገኘ መምጣቱን ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።
አደገኛ ቦዘኔነትንና እየተበራከተ የመጣውን የጎዳና ተዳዳሪነትን ችግር ለመቀነስ የፖሊስ አባላቱ በየጊዜው እየተገናኙ በመመካከርና መፍትሄ በማፈላለግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የፖሊስ አባሎቹ የአካባቢያቸውን ሰላምና ደህንነት በመጠበቅ፣ ወንጀለኞችን ለህግ በማቅረብ፣ ወንጀልና ኮንትሮባንድን በጋራ ለመከላከል የጀመሩትን እንቅስቃሴ አጠናክረው መቀጠላቸውን የገለጹት ኮሚሽነሩ ህብረተሰቡም ከፖሊስ ጎን በመቆም ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል። |
|
|
|
|