የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሶስተኛ ሩብ አመት የስራ ክንውን አፈፃፀም መገምገም ጀመረ

አዲስ አበባ ግንቦት 1/2000/ዋኢማ/ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሶስተኛ ሩብ አመት አገራዊ የስራ ክንውን አፈፃፀም መገምገም ጀመረ።ኮሚቴው በዛሬ ውሎው በዋና ዋና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሲመክር ውሏል።

ዛሬ የተጀመረው የኢህአዴግ ስራ አስፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ ያለፉት ሶስት ወራት የፌዴራል መንግስትን የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት በተመለከተ በጥልቀት ገምግሟል።

በዚህ መሰረት በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች በተለይ ደግሞ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለመፍጠር የተከናወኑ ተግባራትን፣ የመሰረተ ልማት ስራዎች አፈፃፀምን የውጭ ንግድና ኢንቨስትመትን ለማስፋፋት የተካሄደ እንቅስቃሴዎችን እንዲሁም ፌዴራል መንግስት በክልሎች ያከናወናቸው የከተማና የገጠር ልማት ስራዎች ድጋፍ በተመለከተ ሪፖርት ቀርቦ ዝርዝር ውይይት ተካሂዷል።

ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በግምገማው የአገራችን ኢኮኖሚ በተቀመጠለት አቅጣጫ እየተጓዘ ተከታታይና ከፍተኛ እድገት እያስመዘገበ ባለበት በአሁኑ ወቅት የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ሊጐዳ የሚችል የዋጋ ግሽበት መታየቱንና ይህንን ለመቆጣጠር የተቀየሰውን የአጭርና የረጅም ጊዜ መፍትሄ ገምግሟል።

የዋጋ ግሽበቱ ኢኮኖሚያችን ከአለም ኢኮኖሚ ጋር ይበልጥ እየተሳሰረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በአለም ደረጃ የተከሰተው የዋጋ ጭማሪ ተፅእኖ በማሳረፉና የግብይት ስርአታችን ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መገኘት በመሳሰሉ ምክንያቶች የተፈጠረ እንደሆነ ስራ አስፈፃሚው ገምግሟል።

መንግስት ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ በማስቀመጥ ሳይወሰን በዋጋ ግሽበቱ ይበልጥ ለሚጐዱ ወገኖች የኑሮን ሸክም ሊያቃልል የሚችል ድጐማ በስራ ላይ ማዋሉ ጠቃሚ እንደነበር ስራ አስፈጻሚው አረጋግጧል።

ከዚህም በመነሳት መንግስት የዋጋ ግሽበቱ ዘላቂ መፍትሄ እስኪያገኝ ድረስ በአፈፃፀም የታዩ ጉለቶችን ከማስተካከል ጐን ለጐን የተጀመረውን አሰራር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የጋራ ግንዛቤ ተይዞበታል።

ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በቴሌኮሚኒኬሽን፣ በኤሌትሪክ ሃይል አቅርቦት፣ በመንገድና ውሃ መሰረተ ልማት አውታሮች ግንባታ ረገድ ቀደም ሲል የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እየቀጠሉ እንደሆነ አረጋግጧል፤

ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የቴሌ ኮም አቅም ግንባታ ባሃገር ውስጥ አገልግሎቱን ለማስፋፋት የተካሄደው ጥረት በአጭር ጊዜ በገጠርና በከተማ የቴሌኮሚኒኮሽን ሽፋንን ለማስፋት እንዳስቻለ በማረጋገጥ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ አገልግሎትን ከማስፋፋት በተጨማሪ ጥራቱን ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መረባረብ እንዳለበት ስምምነት ላይ ደርሷል።

የኤሌትሪክ ሃይል አቅርቦትን በተመለከተ በሃገራችን አገልግሎቱን ለሚሹና መጠቀም የጀመሩ ኢንዱስትሪዎች በመበራከታቸው ፤ ገጠር የኤሊክትሪክ ስርጭት መስፋፋት እንዲሁም በዘንድሮ የዝናብ መዘግየት በመከሰቱ የተነሳ የአቅርቦት እጥረት ማጋጠሙን ተመልክቷል።

መንግስት ካለፉት አመታት ጀምሮ በተከዜ፣ በግልገል ግቤ ሁለትና በጣና በለስ ወንዞች ላይ ከ1200 በላይ ሜጋ ዋት በላይ ለማመንጨት የሚያስችሉ ግንባታዎችን ሲያካሄድ የቆየ በመሆኑና ግንባታቸው በመጠናቀቅ በመቃረቡ ረጅም በማይባል ግዜ በአስተማማኝ ሁኔታ ወደሚቀረፍበት ምእራፍ እንደምንገባ አረጋግጧል።

በተመሳሳይ ሁኔታ የመንገድ ግንባታው ተጠናክሮ መቀጠሉን ያመከለተው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በከተሞች የውሃ አቅርቦትን ለማሻሻልና ለማስፋት እየተወሰደ ያለውን እርምጃም በስፋት ገምግሟል። ከተሞቻችን እየተሻሻሉና እየተስፋሱ ከመሄዳቸው ተያይዞ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ጉዳይ በከፍተኛ ፍጥነት ማስፋፋት እንደሚገባ የጋራ ግንዛቤ የተያዘ ሲሆን በዚህ ረገድ የተጀመሩ ስራዎች አቅም በፈቀደ መጠን ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።

የውጭ ንግድና ኢንቨስትመንትን በፍጥነት እየተስፋፋ እንደሆነ ያረጋገጠው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባሳለፍነው ዓመት ሃገራችን ወደ ውጭ ከላከችው ምርት ያገኘችው የውጪ ምንዛሪ ገቢ ጉልህ ጭማሪ ማሳየቱን ገልጿል። በተጨማሪ የውጭ ኢንቨስተሮች በሃገራችን ያላቸው ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና እየተስፋፋ መምጣቱን አመልክቶ በሁለቱም መስኮች የተጀመረው ጥረት ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ወስኗል።

ፌዴራል መንግስት ለክልሎች ሲሰጠው የቆየው ድጋፍ ባለፈው ሶስት ወራትም ተጠናክሮ መቀጠሉን የገመገመው ስራ አስፈጻሚው በዚህ መሰረት በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርትና መልካም አስተዳደርን በማስፈን ላይ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀሱን አመልክቶ በዚህ ረገድ የተገኙ መልካም ልምዶችን ለማስፋፊትና መላውን ገጠር የሚሸፍኑ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።

በከተሞች የተጀመሩ የዘመናዊ ቁጠባ ቤቶች ግንባታና የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንዱስትሪዎች ልማት ለማስፋፋት ሲካሄድ የቆየው ጥረት ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ወስኗል።

የሶስተኛ ሩብ አመት አገራዊ የስራ ክንውን አፈፃፀም በመገምገም ላይ ያለው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ ነገም ቀጥሎ የሚውል ሲሆን እስከ መስከረም የሚኖሩ ሰራዎችን የአፈፃፀም አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።