ለውሃ ማጣሪያ የሚያገለግል ንጥረ ነገር የሚያመርት ፋብሪካ የማምረት ስራ መጀመሩን ገለጸ

አዲስ አበባ ግንቦት 1/2000/ዋኢማ/ ለውሃ ማጣሪያ የሚያገለግል ንጥረ ነገር የሚያመርትና በ9 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የተገነባ ፋብሪካ የማምረት ስራ መጀመሩን የቢሻንጋሪ ማጣሪያ ኢንዱስትሪዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አስታወቀ።

የማህበሩ የህዝብ ግንኙነት መኮንን አቶ አብርሃ ኃይለሚካኤል ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፤ በሞጆ የተገነባው ፋብሪካ በአመት 58 ነጥብ 4 ሚሊየን ምጥን የውሃ ማጣሪያ ንጥረ ነገር የማምረት አቅም አለው።

ማጣሪያው በውሃ ውስጥ የሚገኙ በሽታ አምጪ ተህዋስያንን በመግደልና ውሃን በማጣራት ሰዎችን ከውሃ ወለድ በሽታዎች እንደሚከላከል ገልጸው፤ ባለሃብቶቹ በባለሙያ የተሰጣቸውን ምክር በመቀበል በመስኩ መሰማራታቸውን ተናግረዋል።

ፋብሪካው በአይነቱ የመጀመሪያ እንደሆነና ለ65 ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠሩን አመልክተው፤ የውሃ ማጣሪያ ንጥረ ነገሩን በዝቅተኛ ዋጋ ለህብረተሰቡ ለማዳረስ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ንጽህናው የተጠበቀን ውሃ ለህዝቡ ለማዳረስ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑንና በአገሪቱ ብዙ ህዝብ ንጽህናው ያልተጠበቀ የወንዝና የጉድጓድ ውሃ ለመጠጥ እንደሚጠቀም ገልጸው፤ ፋብሪካው የሚያመርተው ንጥረ ነገር በተለይም በገጠር ለሚኖሩ ህዝቦችና ለስራ ለሚንቀሳቀሱ ዜጎች አገልግሎት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።

ፋብሪካው የናሙና ምርቱን እያመረተ መሆኑንና ምርቱ በኢትዮጵያ ስነ ምግብ ምርምር ኢንስቲትዩት ምርመራ እየተደረገበት መሆኑን ያመለከቱት የህዝብ ግንኙነት መኮንኑ፤ ውጤቱ እንደታወቀ በሙሉ አቅሙ ማምረት እንደሚጀምር መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።