በትግራይ ደቡባዊ ዞን የግንቦት 20 በዓልን በድምቀት ለማክበር እንቅስቃሴ ተጀመረ

መቀሌ ግንቦት 2/2000/ዋኢማ/ አምባገነኑ የደርግ አገዛዝ የተገረሰሰበትን የግንቦት 20 በዓል በትግራይ በደቡባዊ ዞን በልዩ ድምቀት ለማክበር እንቅስቃሴ መጀመሩን የዞኑ አስተዳድር አሰታወቀ።

የዞኑ አስተዳዳሪና የበዓሉ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ሃይለ አስፈሃ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፤ የዘንድሮውን የግንቦት 20 በዓል ከሚሌኒየሙ በዓል ጋር በማያያዝ በክልል ደረጃ በትግራይ ደቡባዊ ዞን ከወሩ መግቢያ ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

በዓሉን ለማድመቅ የፀጥታ፣ የቅስቀሳ፣ የባዛርና ኤግዝብሽን፣ የባህልና ስፖርት ኮሚቴዎች የሚገኙባቸው ስምንት ኮሚቴዎች ተቋቁመው ሥራቸውን ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን በማከናወን ላይ መሆናቸውን አስተዳዳሪው አአስታውቀዋል።

በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎችና ቀበሌዎች ደረጃ ከግንቦት 12 እስከ 17/2000 ድረስ ባለፈው መራራ የትግል ወቅትና አሁን በተገኘው የሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ስርዓት የተገኙ ድሎች ዙሪያ ውይይት እንደሚካሄድና ህብረተሰቡም በትግሉ ወቅት የተሰው ጀግኖችን መቃብር የማጠርና የመንከባከብ ስራ እንደሚያካሄድ ገልጸዋል።

በዓሉ በደቡባዊ ዞን እንዲከበር የተመረጠበት ምክንያት የዞኑ ህዝብ በጣሊያን ወረራ ወቅትና ከዚያ በኋላ በነበሩት ጨቋኝ አገዛዝ በመቃወም ያደረገውን ትግል እንዲሁም ግንቦት 19/1981 ደርግ በማይጨው ከተማ አከባቢ ከባድ ውጊያ አድርጎ ከፍተኛ ሽንፈት የተከናነበትን ቀን ለማስታወስ እንደሆነ አስረድተዋል።

በበዓሉ ዋዜማ በማይጨው፣ ኮሮም፣ አለማጣና ሌሎች ከተሞች በወቅታዊና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ የፓናል ውይይቶችና ሰላማዊ ሰልፎች እንደሚካሄዱ አስታውቀዋል።

የማይጨው ከተማ አስተዳድር ማስታወቂያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወልዱ መሓሪ በበኩላቸው፤ በከተማው የሚገኙት በ220 ሚሊየን ብር የተገነባው ችቡድ ፋብሪካ፣ በ3 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር የተገነባው ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤትና የአትሌቲክስ መንደር በዓሉን ምክንያት በማድረግ እንደሚመረቁና ህዝቡም በዓሉን በላቀ ደምቀት ለማክበር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል።

ከከተማው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ሰሰን መኮንንና አቶ ይትባረክ ደስታ በሰጡት አስተያየት፤ ነዋሪው እንግዳ ተቀባይነቱን በግንቦት 20 በዓል በተግባር ለማሳየት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።