ዳሎል ግንቦት 2/2000/በአፋር ክልል የሚገኙ የሐዞ ሰማየና ሀስቦ ጎሳዎች አዲሱን ሚሊኒየም ምክንያት በማድረግ በታላቅ ድምቀት በተከበረው በዓል ላይ አዲስ ባህላዊና ሃይማኖታዊ መሪ ሾሙ ።
በዚሁ የፌደራልና የአጎራባች ክልሎች የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት፣ የጎሳዎቹ አባላትና፣ከጅቡቲና ከኤርትራ ሽመልባ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ የመጡ ኤርትራውያን እንግዶች በተሳተፉበት ከትናንት በስቲያ በዳሎል ወረዳ አንዲብ ቀበሌ በተከናወነው በዓል ላይ የተሾሙት "አና" መሐመድ ዑመርመሐመድ ናቸው ።
በባህሉ መሠረት የመጨረሻው "አና" የደጃዝማች ዑመር መሐመድ ኢስማኤል ልጅ ሲሆኑ የሳቸው መሾም እንደታወጀ የጎሳዎቹና የንዑሳን ጎሳዎች መሪዎች ወደ መድረኩ እየቀረቡ አዲሱ መሪያቸው በደስታ እንደተቀበሉትና ወደ ሰላምና ብልጽግና እንደሚመሯቸው ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል ።
የባህልና ቱሪዝም ሚነስቴር ሚኒስትር ዴኢታ አቶ መሐመድ ገዓስና የትግራይ ክልል መንግሥት ተወካይ አቶ ጎበዛይ ወልደአረጋይ በበአሉ ላይ ተገኝተው ባሰሙት ንግግር ጎሳዎቹ በአከባቢው ሰላምና ዕድገት ለማምጣት የሚያስችላቸውን መሪ በመምረጣቸው ያላቸውን ድጋፍና መልካም ምኞች ገልጸዋል ።
የአከባቢው ጎሳዎች በዓሉን ያከበሩበት ዓላማ ባህላዊና ሃይማኖታዊ መሪያቸውን ከመሾም ባሻገር የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ያስቀመጠውን ቋንቋንና ባህልን ጠብቆ ለትውልድ የማስተላለፍ መብት ለማረጋገጥ መሆኑን በበዓሉ ሥነ ስርዓት ላይ ተገልጿል ።
እንደዚሁም ጎሳዎቹ ከአጎራባች ክልሎችም ሆነ ከሌሎች ተመሳሳይ የአፋር ጎሳዎች ጋር ያላቸውን ዝምድና ለማጎልበትና የሺ ዓመታት ታሪክ ያለውን "ሳኩዕ ነጋሪት" የተሰኘ የሃገር ቅርስ እገረ መንገዳቸው ለማስተዋወቅ የበዓሉ መከበሩ አስፈላጊ እንደሆነ ተመልክቷል ።
ይኸው በዓፋር ክልል በሚገኙ ጎሳዎች ለዘመናት በታላቅ ድምቀት ሲከበር የኖረ ሲሆን በተለያዩ ምክንያቶች ከ1968 ዓመተምሕረት ወዲህ ግን ባህላዊና ሃይማኖታዊ መሪያቸው ሳይሾሙ መቆየታቸውን ተጠቅሷል ።
በበዓሉ ላይ እንደተመለከተው የሐዞ ሰማየና ሀስቦ ጎሳዎች አዲስ ባህላዊና ሃይማኖታዊ መሪ የሚሾሙት ነባሩ መሪያቸው ከሞተ በኋላ ከመጀመሪያ ሚስት የተገኘ ወንድም ሆነ ሴት የበኩር ልጅ ብቻ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል ሲል ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።