በኦሞ ወንዝ ሙላት ተፈናቅለው የነበሩ አርብቶ አደሮች ራሳቸውን ቻሉ

ጂንካ 2/2000/ዋኢማ/በደቡብ ኦሞ ዞን በዳሰነች ወረዳ በ1998 ዓ.ም በኦሞ ወንዝ ሙላት የተፈናቀሉ አርብቶ አደሮች መንግስትና ህዝብ በወቅቱ ፈጥነው ስላቋቋሙን ራሳችንን እየቻልን ነው አሉ፡፡

አርብቶ አደሮቹ እንደገለጹት ባለፈው ነሀሴ ወር 1998ዓ.ም በኦሞ ወንዝ ሙላት በተፈናቀሉበት ወቅት መንግስትና ህዝብ ፈጥነው በመድረስ ምግብ፣አልባሳት፣ምርጥ ዘርና ልዩ ልዩ ግብአቶችን ባንድ ላይ በማቅረብ ስላቋቋማቸው ባሁኑ ሰአት የአገዳ ሰብል፣ የቅባት እህሎችና ፈጥነው ለምግብነት የሚውሉ ስራ ስሮችን እያመረቱ ራሳቸውን በመቻል ላይ ይገኛሉ፡፡

ከአርብቶ አደሮች መካከል አቶ ቶርፎሲያ ኮሮ እና አቶ ይርቡር ማረቃ በሰጡት አስተያየት የኦሞ ወንዝ ዳር እየተከተሉ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ የማሽላ ምርት ያመርቱ ከነበሩበት ተላቀው በአሁኑ ሰአት በመስኖ በመታገዝ በቆሎ፣ማሽላ፣ሰሊጥ፣ለውዝ፣በርበሬ፣ጎደሬ፣ካዛባ እና የመሳሰሉትን በማምረት ለገበያ በማቅረብ ብዙ ከብቶችን በመግዛት ሀብት ለማፍራት ችለዋል፡፡

የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ያስቻለን በመስኖ በመታገዝ በማንኛውም ወቅት እንድናመርት ከወረዳው አርብቶ አደር ልማት ጽ/ቤት የውሀ ፓምፕ በመመደቡ እና የልማት ጣቢያው ሰራተኞች ቀንና ማታ ሳይለዩን ትምህርትና ምክር በመስጠታቸው ነው ያሉት አርብቶ አደሮቹ ፣እስካሁን ካመረትነው በላይ እንድናመርት እና ወደ መሀል አገር ገበያ ምርታችንን ማቅረብ እንድንችል መንግስት ተጨማሪ የውሀ ፓምፕ እንዲረዳን እንጠይቃለን ብለዋል፡፡

የልማት ጣቢያ ሰራተኞች የሆኑት ወ/ሪት ሙሉነሽ ቱኩዬ እና አቶ ራጉኤል ኢታ በጋራ በሰጡት አስተያየት አርብቶ አደሮቹ እራሳቸውን ለመለወጥ እና ለማምረት ያላቸውን ፍላጎት የበለጠ እንዲሰሩ እንዳተጋቸውና በለውጡ በጣም እንደተደሰቱ ተናግረዋል፡፡

የዳሰነች ወረዳ አርብቶ አደር ልማት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ በላይ መተኪያ በአሁን ወቅት በ150 ሄክታር ላይ 600 የሚሆኑ አርብቶ አደሮች በመስኖ በመታገዝ እያለሙ መሆናቸውን ገልጸው የአርብቶ አደሮቹ ኑሮ ለውጥ እያሳየ መምጣቱ ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል፡፡

የአርብቶ አደሮቹን የተጨማሪ የውሃ ፓምፕ ጥያቄ ለመመለስ ጥረቶች እያደረግን ነው ብለዋል፡፡

እንዲሁም በመልሶ ማቋቋም ፕሮግራም በኦሞ ወንዝ ዙሪያ በ25 ቀበሌዎች የሚኖሩ ከ30ሺ በላይ አርብቶ አደሮች በ350 ሄክታር መሬትላይ በመስኖ ልማት ለማሳተፍ መታቀዱን አቶ በላይ ገልጸዋል፡፡

ይህንን እቅድ ለማሳካትና አርብቶ አደሩን ከርባታው ጎን ለጎን የእርሻ እንቅስቃሴውን ከፍ ለማድረግ የሰብልና የመኖ ዘር ግዢ ተፈጽሞ በመጓጓዝ ላይ ነው ማለታቸውን የደቡብ ኦሞ ዞን ማስታወቂያ እና ባህልን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡