በደቡብ ከ21 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች እየተንቀሳቀሱ ነው

አዲስ አበባ ግንቦት 2/2000/ዋኢማ/ በደቡብ ክልል ከ21 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን የክልሉ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ገለፀ።ከ450ሺ በላይ ዜጎች የስራ እድል ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

የኤጀንሲው ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ አዳማ ትንጰዬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ኤጀንሲው የኢንቨስትመንት ፈቃድ የሰጠው በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሳተፍ ፈቃድ ለጠየቁ 3ሺ 125 የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ነው።

ባለሀብቶቹ ፈቃዱን የወስዱት በግብርና፣ በአግሮ ኢንዱስትሪ፣ በሪል ስቴት፣ በኮንስትራክንሽን፣ በሆቴልና ቱሪዝምና በሌሎች አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ዘርፍ ለመሰማራት ነው።

የኢንቨስትመንት ፈቃድ ካገኙት መካከል 85 የሚሆኑት የውጪ ሀገር ዜግነት ያላቸው ሲሆኑ ቀሪዎቹ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች መሆናቸውን ገልፀዋል።

ባለሀብቶቹ የግንባታና ሌሎች ቅድመ ዝግጅቶችን አጠናቀው ወደ ስራ ሲገቡ ለ450ሺ 39 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ጠቁመው፤ ይህም የስራ አጥ ቁጥርን ከመቀነስ አንፃር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊኖረው እንደሚችል አስገንዝበዋል።

ፍቃድ ካገኙት መካከል አንዳንዶቹ ግንባታቸውን አጠናቀው ወደ ስራ የገቡ ሲሆን ባለሃብቶቹ በተሰማሩበት መስክ የውጪ ምንዛሪ ከማስገኘት ጀምሮ ለአካባቢያቸው ልማት አስተዋፆ እያደረጉ መሆናቸውን አቶ አዳማ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የክልሉ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ሌሎች ባለሀብቶችን ወደ ክልሉ ለመሳብ አጠቃላይ የክልሉን የኢንዱስትሪ አቅም የሚያሳይ ጥናት ማድረጉን ገልፀው፤ ከተጠናው ጥናት ውስጥ ከሰባት መቶ በላይ የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች መለየታቸውንና ከ300 በላይ ለሚበልጡ ኢንዱስትሪዎች የፕሮጀክት ፋይል መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

እንዲሁም ከ530 ሺ በላይ ካሬ መሬት ተከልሎ ለባለሀብቶች መዘጋጀቱን አቶ አዳማ መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።