አዳማ ግንቦት 2/2000/ዋኢማ/ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ 70 ወረዳዎች ለግብርና ምርት ግብይት ማሻሻያ ፕሮግራም ከ117 ሚሊየን ብር በላይ ተመድቦ ተግባራዊ እንቅሰቃሴ መጀመሩን የክልሉ ግብርና ምርት ገበያ ኤጀንሲ አስታወቀ። በተያዘው ዓመት በፕሮግራሙ 50ሺ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ተገልጿል።
በኤጀንሲው የግብርና ምርት ግብይት ማሻሻያ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ተማም አባ ቡልጉ በግብይቱ ማሻሻያ ላይ ለስድስት ቀናት በአዳማ ከተማ የተዘጋጀው ስልጠና ዛሬ ሲጠናቀቅ እንደገለጹት በጀቱ የተመደበው ለአቅም ግንባታ ስልጠና፣ለገጠሩ አርሶ አደሮች ብድር አገልግሎት እንዲሁም ፕሮግራሙ ማስተባበሪያ ለተለያዩ ጉዳዮች ይውላል።
የፕሮግራሙ ዋና ዓላማ የግብርና ምርት ገበያ ከአርሶ አደሩ መንደር እስከ ዓለም ገበያ ድረስ ማስተሳሰር በሚቻልበትና አርሶ አደሩ በገበያ ላይ አዋጪነት ያላቸውን ሰብሎች በጥራትና በብዛት እንዲያመርት ለማበረታታት የተዘጋጀ መሆኑን አመልከተዋል።
ባለፈው ዓመት በተጀመረውና ለሰባት ዓመታት በሚቆየው የግብርና ልማት ማሻሻያ ፕሮግራም በክልሉ የሚገኙ 70 ወረዳዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸው ከእነዚህም መካከል በተያዘው ዓመት በ18 ወረዳዎች 50ሺ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስታወቀዋል።
ለፕሮግራሙ ማስፈፀሚያ የዓለም አቀፍ ግብርና ፌንድ/IFAD/ ከመደበው በጀት ውስጥ 70 በመቶ ያህሉ የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታመነትን ለማሳደግ በብድር የሚሰጥ መሆኑንም አስተባባሪው ተናግረዋል።
ፕሮግራሙ በአገር አቀፍ ደረጃ ኦሮሚያን ጨምሮ በስድስት ክልሎች በሚገኙ 200 ወረዳዎች ለተከታታይ ሰባት ዓመታት እንደሚካሄድ አስተባባሪው አስታውቀዋል።
ለስድስት ቀናት በቆየው የግብርና ምርት ግብይት ስልጠና ላይ ከአምስት የኦሮሚያ ወረዳዎች የተውጣጡ 65 በግብርና ምርት ግብይቱ ልዩ ተዋናይ የሆኑ አርሶ አደሮች፣ የልማት ሰራተኞች የየወረዳዎቹ ግብርና ጽህፈት ቤቶች፣ነጋዴዎችና የማህበራት ማደራጃ ጽህፈት ቤት የሥራ ሀላፊዎች መሆናቸውን መሳተፋቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።