በቤንች ማጂ ዞን ባለሀብቶች ከአንድ ቢልየን ብር በሚበልጥ ወጭ የተለያዩ የልማት ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑ ተገለፀ

ግንቦት 2/2000 (ዋኢማ) ቤንች ማጂ/ በደቡብ ክልል በቤንች ማጂ ዞን ያለውን ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጭ በመጠቀም ባለሀብቶች ከአንድ ቢልየን ብር በሚበልጥ ወጭ የተለያዩ የልማት ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑን የዞኑ ንግድና ኢንዱስትሪ መምሪያ አስታወቁ፡፡

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ሰለሞን ወንድሙ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ በእርሻ፣ ኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች የተሰማሩ 89 ባለሀብቶች አንድ ነጥብ አንድ ቢልዮን ብር መድበው በመስራት ላይ ናቸው፡፡

በዞኑ በቡናና ቅመማ ቅመም፣ በጎማ ዛፍ ልማት፣ በንብ ማነብ፣ በእንስሳት እርባታና በሰብል ልማት ዘርፍ 6 ሺ 777 ሄክታር መሬት ላይ 46 ባለሀብቶች ተሰማርተው የማልማት ተግባር እያከናወኑ መሆኑንም ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

በእሸት ቡና መፈልፈልና ማዘጋጀት፣ በደረቅ ቡና የማበጠር የኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ 24 ባለሀብቶች ደግሞ ምርታቸውን ለገበያ በማቅረብ ላይ እንደሆኑም አቶ ሰለሞን አስረድተዋል፡፡

እንዲሁም በሆቴል፣ ክሊኒክ፣ ትምህርት ቤት፣ ነዳጅ ማደያና በሪል እስቴት ዘርፎች 19 ባለሀብቶች ተሰማርተው አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በዞኑ በእርሻው፤ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት መስጫ ዘርፎች የተፈጠረው የኢንቨስትመንት መስክ ለ94ሺ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠሩን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።

በዞኑ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጮች የበለጠ በማስተዋወቅ በዘርፉ በርካታ ባለሀብቶች እንዲሰማሩ ለማስቻል የሚረዳ ፎረም በቅርቡ በሚዛን ከተማ ለማካሄድ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የገለፁት ኃላፊው በዞኑ ብቻ የሚገኙ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በስፋት የማስተዋወቅ ተግባራት ላይ ትኩረት እንደሚሰጥም ተናግረዋል፡፡

በቤንች ማጂ ዞን 10 ወረዳዎች በሚገኙ በገጠርና የከተማ ቦታዎች ከ105 ሺ ሄክታር የሚበልጥ መሬት ለኢንቨስትመንት እንደሚውል በጥናት እንደተረጋገጠ አቶ ሰለሞን መግለፃቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡