የዓለም አቀፍ የኢህአዴግ ደጋፊዎች ፎረም ግንዛቤ የማሳደግ ተግባር እያከናወነ ነው

አዲስ አበባ ግንቦት 2/2000/ዋኢማ/ በአሜሪካን የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ውስጥ በመካሄድ ላይ ስላሉት ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ለውጦች በቂ ግንዛበ ኖሯቸው ለአገሪቱ ልማት የበኩላቸውን መወጣት እንዲችሉ የቅስቀሳ ስራ በመስራት ላይ መሆኑን የዓለም አቀፍ የኢህአዴግ ደጋፊዎች ፎረም አስታወቀ።

የፎረሙ ሊቀመንበር ኢንጂነር መኮንን ካሳ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደተናገሩት፤በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአገሪቱ ያሉትን ለውጦች እንዲገነዘቡ ለማስቻልና መንግስት እያከናወናቸው ያሉትን ዋና ዋና ተግባሮች ለማስተዋወቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢህአዴግ ደጋፊዎች ፎረም መስርተዋል።

ፎረሙ በኢትዮጵያዊያን መካከል በፖሊቲካ ዙሪያ ያሉትን ልዩነቶች በውይይት የመፍታት ባህልን ለማሳደግ የሚያስችሉ የውይይት መድረኮች በማዘጋጀት፣ ኢህአዴግ ፖሊስውን እንዲያስተዋውቅ የማድረግ ስራ እየሰራ ነው፡፡

ኢትዮጵያን በተመለከተ በሌሎች አገራት የሚወጡት ፖሊስዎችና በተሳሳተ መረጃ ላይ የተመሰረቱ ሪፖርቶችን የማስተካከልና ወደ አንድ ጎን ያላጋደሉ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ በመስራት ላይ መሆኑን ሊቀመንበሩ አስረድተዋል።

አሜሪካን የሚሰባሰቡ የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚዎች በአገሪቱ ያለውን ዘርፈ ብዙ ለውጦችን በተሳሳተ መልኩ በማቅረብ የፈጠሩትን የተሳሳተ ግንዛቤ ለማስተካከል የሚያስችል ስራ በመስራት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ተቃዋሚዎች የአገሪቱን ሕገ መንግስት ለመናድ መንቀሳቀሳቸው በፍርድ ቤት በመረጋገጡ፣ በአገሪቱ ዴሞክራሲ እንደሌለና ሰብኣዊ መብት ረገጣ እንዳለ በማስወራት የስልጣን ጥማታቸውን ለመወጣትየአገር ስም የማጉደፍ ስራ መስራታቸውን ያስታወሱት ሊቀመንበሩ በዚህ ምክንያት አሜሪካን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለተቃዋሚዎች ድጋፍ በመከልከል የኢህአዴግን ማንነትን በመረዳት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ፎረሙ ከተቋቋመበት ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ ባደረገው እንቅስቃሴ በአምስት ከተሞች ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ያቋቋመ ሲሆን፤ በካናዳ ፣ስዊድን እና በሌሎች አገራት ለማቋቋም በእንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያ በአገሪቱ ልማት ላይ ተሳትፎ በማድረግ ራስንም አገርን ለመጥቀም የሚችሉባቸውን አማራጮች በማስተዋወቅ ላይ እንደሆኑ ገልጸዋል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በሙያቸው ለመደገፍ የሚችሉትን በመመልመል ለአገሪቱ ልማት የበኩላቸውን እንዲወጡ የማሰተባበር ስራ መጀመራቸውን ኢንጂኒየር መኮንን ተናግረዋል።

አክለውም የኢህአዴግ ደጋፍዎች ፎረም በማድረግ ላይ ካለው እንቅሰቃሴ በተጓዳኝ በኢንተርነት በሚደረግ ውይይት የኢህአዴግን ፖሊስዎችና በአገሪቱ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የሚያስተዋውቁ ሌሎች ቡድኖችም መፈጠራቸው አመልክቷል።

የኢህአዴግ ደጋፍዎች ፎረም ባለፉት አራት ወራት ውስጥ በኢንተርነት ባደረገው የአባላት ምዝገባ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን በአባልነት መመዝገብ መቻሉን ኢንጂኒየር መኮንን መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።