መንግስት ለግል ኢንቨስትመንት መጠናከር ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ ግንቦት 3/2000/ዋኢማ/ መንግስት ለግል ኢንቨስትመንት መስፋፋት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አስታወቁ። በ10 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ተግባራዊ በመሆን ላይ የሚገኘው የካስቴል ወይን እርሻ ትናንት ተመረቀ።

ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ታደሰ ኃይሌ የወይን እርሻውን በመረቁበት ወቅት እንዳስታወቁት፤ የኢትዮጵያ መንግስት ለግል ኢንቨስትመንት አመቺ የሆኑ ፖሊሲዎችንና እስትራቴጂዎችን ተግባራዊ በማድረግ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው እንዲጠናከር ተገቢውን ድጋፍ መስጠቱን ይቀጥላል።

መንግስት ኢንቨስትመንትን ለማሳደግና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማስመዝገብ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን የገለጹት አቶ ታደሰ፤ አሁን እየተጠናከረ የመጣው የኢንቨስትመንት ፍሰት አገሪቱ ትክክለኛ የኢኮኖሚና አመቺ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ እንዳላት የሚያመለክት መሆኑን ተናግረዋል።

በዓለም በወይን ምርት የታወቀውና በሚስተር ፔየር ካስቴል የሚመራው ኩባንያ በኢትዮጵያ በወይን ምርት ለመሰማራት መወሰኑ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ረገድ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል።

የተመረቀው የወይን እርሻ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው መሆኑን ያመለከቱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ መንግስት ባለሃብቱ በኢትዮጵያ ለሚያደርጉት የልማት እንቅስቃሴ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱንና ለበለጠ ስኬታማነት ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሚስተር ስቴቨን ጎንበሬት በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ሊሰሩባት ለሚፈልጉ ባለሃብቶች የዕድል አገር መሆኗን ተናግረዋል።

መንግስት የፈረንሳይ ባለሃብቶች ወደ አገሪቱ በመምጣት መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ በይፋ ጥሪ ማድረጉን ያስታወሱት አምባሳደሩ፤ የፈረንሳይ ባለሃብት በወይን ልማትና በወይን ጠጅ ምርት በመሰማራታቸው መደሰታቸውንና አገሪቱ በአበባ መስክ እንዳሳየችው እድገት ሁሉ በወይን መስክም እንደምታስመዘግብ እምነታቸውን ገልጸዋል።

የካስቴል ወይን ጠጅ ፋብሪካ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ዋና ስራ አስኪያጅ ሚስተር ጆን ፖል ብላቭየር በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ማህበሩ የወይን ልማቱን የሚያከናውነው በዝዋይ ከተማ የቀድሞው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ድርጅት እርሻ በነበረ 495 ሄክታር መሬት ላይ ነው።

ማህበሩ በኢትዮጵያ ለወይን ምርት ተስማሚ የሆኑ በርካታ አካባቢዎች መኖራቸውን ማረጋገጡን ጠቁመው፤ ስራውን ለመጀመር ግን ዝዋይ ተመራጭ ሆኖ መገኘቱን አመልክተዋል።

የቀድሞው የአትክልትና ፍራፍሬ ሰራተኞች በወይን ልማቱ ውስጥ እንዲቀጥሉ መደረጉንና ለቀይና ነጭ ወይን ጠጅ ምርት የሚውሉ ችግኞች እንደሚለሙ ገልጸው፤ በልማቱ ለ50 ቋሚና ለ200 ጊዜያዊ ሰራተኞች የስራ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

ከሦስት ዓመታት በኋላ የወይን ጠጅ ማምረቻ ማሽኑ ማምረት ሲጀምር እስከ 1ሚሊየን ጠርሙስ የወይን ጠጅ በማምረት 50 በመቶ ያህሉን ለአገር ውስጥ ገበያና ቀሪውን 50 በመቶ ደግሞ ለውጭ ገበያ የማቅረብ ዕቅድ እንዳለው ጠቁመዋል።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የፌደራልና የኦሮሚያ ክልል የስራ ኃላፊዎችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች የተገኙ ሲሆን፣ አቶ ታደሰ ኃይሌ የወይን እርሻውን የመጀመሪያ ችግኝ መትከላቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።