የጨፌ ሴት አባላት የሴቶችን መብቶች ለማስከበርና የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ተገለፀ

አዳማ ግንቦት 2/2000/ዋኢማ/ የጨፌ ሴት አባላት የሴቶችን መብቶች ለማስከበርና የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ግንባር ቀደም ሚና መጫወት እንደሚገባቸው የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ አስታወቁ። በሥርዓተ ፆታና አመራር ላይ ያተኮረ ስልጠና በአዳማ ከተማ አባ ገዳ አደራሽ ተጀምሯል።

አፈ ጉባኤው ዶክተር መሐመድ ሐሰን በሥርዓተ ፆታና አመራር ዙሪያ የተዘጋጀው ስልጠና ትናንት በአዳማ ከተማ አባ ገዳ አደራሽ ሲጀምር እንደገለፁት፤ የጨፌ ሴት አባላት የሴቶችን ሁለንተናዊ መብቶችን ለማስከበርና ከወንዶች ዕኩል የልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ የተሰጣቸውን ሀላፊነት ሊወጡ ይገባል።

ሴቶች ባለፉት ሥርዓቶች አስታዋሽ አጥተው መቆየታቸውንና በአሁኑ ጊዜ ሕገ-መንግስቱ የሰጣቸውን መብቶች እንዲጠቀሙና ፍላጎታቸው እንዲሟሉ ለማድረግ የጨፌ ሴት አባላት በሚኖሩባቸው ወረዳዎችና ቀበሌዎች ሁሉ ሴቶችን በማነሳሳትና በማደራጀት ከጎጂ ልማዶች ተጠብቀው የልማት ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማስቻል መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ከሶስት ዓመታት በፊት በተካሄደው ምርጫ ጨፌው ከሚፈልገው 537 መቀመጫዎች መካከል 39 በመቶው በሴቶች እንዲሸፈኑ መደረጉን ያስታወቁት አፈ ጉባኤው፤ የሴቶቹ ተሳትፎ ማደግ የጨፌው ስልጣንና ሥራ ከግቡ እንዲደርስ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የጎላ ነው ብለዋል።

የጨፌ ሴት አባላትም ሆኑ በተለያዩ ኦሮሚያ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ በአመራር ደረጃ ላይ ያሉ ሴቶች በወጡት ሕጎችና ደንቦች ላይ በመመስረት ቀደም ሲል ያደርጉት ከነበሩት በላይ ለፆታና ለመብቶች እኩልነት መረጋገጥ በጋራ ተቀናጅተው በመሥራት የሴቶችን ተጠቃሚነት መከታተልና መቆጣጠር እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

ቀደም ሲል በክልሉ ይታዩ የነበሩትን ሁለገብ ችግሮች ለማስወገድ በተደረገው ጥረት ባለፉት ሁለት ዓመታት ለጨፌ አባላት በልማት፣በሰላም፣በመልካም አስተዳደር፣ በዴሞክራሲ ግንባታና የህግ የበላይነት ሥራዎች ላይ የአቅም ግንባታ ስልጠና በመሰጠቱ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣታቸውንና በቀጣይም ስልጠናው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አፈ ጉባኤው አስገንዝበዋል።

ለሦስት ቀናት በሚቆየው ስልጠና ላይ ፆታና ሥርዓተ ፆታ በሀገርና የዓለም አቀፍ ተሞክሮ፣ኮሙኒኬሽን፣ እንዲሁም ኤች አይቪ/ኤድስ በሚሉ ርዕሶች ዙሪያ በባለሙያዎች እንደሚሰጥ ከወጣው መርሀ-ግብር ለማወቅ መቻሉን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።