ባለስልጣኑ ታክስና ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች 8 ቢሊየን 277 ሚሊየን ብር ገቢ ሰበሰበ

አዲስ አበባ ግንቦት 3/2000/ዋኢማ/ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለስልጣን ባለፉት ዘጠኝ ወራት ታክስና ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች 8 ቢሊየን 277 ሚሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን ገለፀ። ገቢው ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ2 ቢሊየን 454 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር ብልጫ እንዳለው አስታውቀዋል።

በባለስልጣኑ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት አገልግሎት ኃላፊ አቶ ገብረመድህን ገብረዮሃንስ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ባለስልጣኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 9 ቢሊየን 518 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 8 ቢሊየን 277 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ችሏል።

ገቢው ከተያዘው እቅድ ጋር ሲነፃፀር 13 በመቶ ያነሰ ቢሆንም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ በ2 ቢሊየን 454 ሚሊየን ብር ብልጫ እንዳለው ገልፀዋል።

ከተሰበሰበው ገቢ ውስጥ ከቀረጥ ነፃ መብት ወደ አገር ውስጥ ከገቡ በኋላ ለሶስተኛ ወገን የዞሩ ተሽከርካሪዎች ለመንግስት ቀረጥና ታክስ እየከፈሉ ሕጋዊ እንዲሆኑ በወጣው መመሪያ መሰረት ባለስልጣኑ ለሶስተኛ ወገን ተላልፈው ከነበሩ 868 መኪናዎች 34 ሚሊየን 812 ሺ 207 ብር በላይ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።

እንዲሁም ኮንትሮባንድን ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረት 105 ነጥብ 20 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው የተለያዩ እቃዎች ወደ ሀገር ሲገቡና ከሃገር ሲወጡ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልፀው፤ በተለያየ መልኩ ሊፈፀሙ ሙከራ ከተደረገባቸው የንግድ ማጭበርበር ድርጊቶችም ከ168 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

ወደ ውጭ ከተላኩ ግምታቸው 1ነጥብ 02 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር የተለያዩ የግብርና ምርቶችን በመላክ አገልግሎት የተሰበሰበ ሲሆን፣ ዋና ዋናዎቹም ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ ጥራጥሬ፣ ጫት፣ አበባ፣ ቆዳና ሌጦ የመሳሰሉት እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለስልጣን በተያዘው የበጀት ዓመት ታክስና ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች 12 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።