የክልሉ ሰራተኞች ስራቸውን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማካሄድ የሚያስችላቸው ስልጠና ማግኘታቸው ተገለፀ

ቡታጅራ ግንቦት/3/2000/ዋኢማ/ በደቡብ ክልል በየዕርከኑ የሚገኙ የአስተዳደር ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎችና ሰራተኞች የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን በተቀላጠፈና ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማካሄድ እንዲችሉ የአቅም ግንባታ ስልጠና ማግኘታቸው ተገለፀ።

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታመነ ተሰማ በቡታጅራ ከተማ ለሰባት ቀናት በተካሄደው የአቅም ግንባታ አውደ ጥናት ላይ እንደገለፁት፤ የሲቪል ሰራተኛውን የማስፈፀም አቅም ለማጐልበትና ተጠያቂነት ያለው አሰራር እንዲሰፍን ለማድረግ የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት ተገቢ ነው።

በመሆኑም በክልሉ ያሉትን የሲቪል ሰራተኞች አቅም ለማሳደግ፣ የአገልጋይነት መንፈስ እንዲዳብር ለማድረግና ውጤታማ ተግባራትን ለማከናወን በተለያዩ ጊዜያት የአቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠቱን ኃላፊው ተናግረዋል።

በሲቪል ሰራተኛው ላይ የአገልጋይነት መንፈስ ሳይሆን የተገልጋይነት መንፈስ በስፋት ዳብሮ መቆየቱን ጠቁመው፤ ችግሩን ለማስወገድ በመጀመሪያ የአስፈፃሚነት ደረጃ ለሚገኙ የዞንና የልዩ ወረዳ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያና በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ግንዛቤ እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።

በክልሉ በተሻሻለው ሕገ-መንግስት ከፍተኛው የአስፈፃሚነት ኃላፊነት የተሰጠው ለርዕሰ መስተዳድሩ ሲሆን፤ መስተዳድሩ ለረዥም ጊዜ በስልጠና ራሱን ያላየበትና ያልፈተሸበት ሁኔታ መኖሩን ከግምት ውስጥ በማስገባት ተከታታይ የአቅም ግንባታ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን አቶ ታመነ አስረድተዋል።

በአቅም ግንባታ ስልጠናው ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ፣ የዞን፣ የልዩ ወረዳና በክልሉ ያሉ የወረዳ የፅህፈት ቤት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች መሳተፋቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።

ስልጠናውን እስከ ቀበሌ ማውረድ ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለው የአመራርና የአስተዳደር ስርዓትን ለመዘርጋት እንደሚያስችል ጠቁመው፤ስልጠናው የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ፅህፈት ቤት ከክልሉ አቅም ግንባታ ቢሮ ጋር በመተባበር እንደተሰጠ አቶ ታመነ መግለፃቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።