ባህርዳር ግንቦት 3/2000 /ዋኢማ/ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደኢህዴን/ 15ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በባህርዳር ከተማ ትናንት በደማቅ ስነ-ስርዓት ተከበረ።
በዓሉ በባህርዳር ከተማ ሙሉዓለም የባህል ማዕከል ሲከበር በባህርዳር ዩኒቨርስቲ የደኢህዴን አደራጅና የበዓሉ አስተባባሪ ተማሪ ጋረደው ጋኒቾ እንደገለጸው፤ በበርካታ ታጋዮች የህይወት መስዋዕትነት የተገኘውን ሰላም ፣ልማትና ዴሞክራሲ ከዳር በማድረስ በአዲሱ ሚሌኒየም ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ወጣቶች የተጣለባቸውን ሀላፊነት ለመወጣት ዝግጁነታቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል ።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኢህአዴግ አጋር ድርጅት አባላት ተማሪዎች ተወካይ ተማሪ ታምራት ተስፋዬ ባስተላለፈው የድጋፍ መግለጫም በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ተጋድሎ የተገኙ ድሎች ዘላቂነት እንዲኖራቸው ወጣቶች የተቀበሉትን ብርቱ ሀላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝቧል ።
የሰሜን ጎንደር መስተዳድር ጽህፈት ቤት ሃላፊና የዞኑ ብአዴን ተወካይ አቶ ሞገስ መኮንን በበኩላቸው በዓሉ በሶስተኛው እልፍ ዓመት የኢትዮጵያን ህዳሴ ለማረጋገጥ በጀመርንበት ማግስት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
በምስረታ በዓሉ ላይ ትግራይ ውስጥ በአፄ ፋሲል ስም ተሰይሞ በሩብ ሚሊየን ብር ለሚሰራው አንድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ተካሄዶ ከ70 ሺ ብር በላይ ገቢ መገኘቱንና ባለፈው ዓመትም በተካሄደው ተመሳሳይ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም 70 ሺ ብር መሰብሰቡ ተገልጿል።
በበዓሉ ላይ የተገኘው የትግራይ ባህላዊ እና የፖሊስ አኬስትራ የኪነት ቡድን የትግሉን ሂደትና ሰማዕታት የሚዘክር ጣዕመ ዜማ ማቅረቡን ዋልታ ኢንፎረሜሽን ማዕከል ዘግቧል።