የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ በቀጣይ ወራት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ በመወያየት መደበኛ ስብሰባውን አጠናቀቀ

አዲስ አበባ ግንቦት 3/2000/ዋኢማ/ ትናንት የተጀመረው የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ በዛሬ ውሎው በመልካም አስተዳደርና በቅርቡ የተካሄደውን የአካባቢና የሟሟያ ምርጫን አስመልክቶ በቀረቡ ሪፖርቶችና በቀጣይ ወራት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ በመወያየት መደበኛ ስብሰባውን ማጠናቀቁ ተገለጸ።

የኢህአዴግ ቃል አቀባይ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፀው፤ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በዛሬ ውሎው እንደልማቱ ሁሉ በመልካም አስተዳደር መስክም መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት በሲቪል ሰርቪስና በፍትህ ስርአት ማሻሻያዎች እንዲሁም በከተማና በገጠር የመልካም አስተዳደር ፕሮግራሞች ዙሪያ ባለፉት አመታት የነበሩትን የአፈፃፀም ችግሮች በመፍታትና ውጤታማ ስራዎችን ለማከናወን ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተደረገው ጥረት ስፋት ሰጭ እንደሆነ ገምግሟል።

በፌዴራልም ሆነ በክልሎች የማሻሻያ ፕሮግራሞቹን በተሟላ መንገድ ለመተግበር እንዲቻል እየተደረጉ ያሉትን ዝግጅቶች በአግባቡ በመምራትና ሂደቱን በማፋጠን መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ወስኖ የአፈፃፀም አቅጣጫዎችንም አስቀምጧል።

የገጠርና የከተማ መልካም አስተዳደር ፓኬጅን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ የተገኙትን መልካም ልምዶች ወደ ሁሉም አካባቢዎች ለማዳረስ የተጀመሩትን ጥረቶች አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው አፅንኦት ሰጥቶ መወያዩቱን ቃል አቀባዩ ገልጿል።

በአገራችን በሚያዝያ ወር የተካሄደው የአካባቢና ማሟያ ምርጫ አፈፃፀምን በሚመለከት በቀረበው ሪፖርት ላይ ባደረገው ውይይትም ኢህአዴግ ወደ ምርጫው ሲገባ አስቀምጧቸው የነበሩት ግቦች በተሟላ መንገድ እንደተሳኩ አረጋግጧል።

ምርጫው ህዝቡ በስፋት የተሳተፈበትና በሁሉም አካባቢዎች ይህ ነው የሚባል ችግር ሳያጋጥም ሰላማዊ በሆነ መንገድ መጠናቀቁን ያረጋገጠው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የአገራችን ህዝቦች በምርጫው ላሳዩት ተሳትፎ ያለውን አድናቆት ገልጿል።

በመራጭነት በመመዝገብም ሆነ በምርጫው ዕለት በየምርጫ ጣቢያው ተገኝቶ በመምረጥ በኩል የታየው የህዝብ ተሳትፎ በመገንባት ላይ የምንገኘው ዴሞክራሲያዊ ስርአት እየጎለበተ መምጣቱን ገልፆ፤ የአገራችን ህዝቦች በህገ-መንግሥቱ የተደነገገውን የሉአላዊ ስልጣን ባለቤትነታቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁነታቸውን ያረጋገጡበት እንደሆነ ስራ ፈስፈፃሚ ኮሚቴው በአንክሮ ተመልክቶታል።

ኢህአዴግ በተወዳደረባቸው የምርጫ ክልሎች በሙሉ መራጩ የኢህአዴግን እጩዎች በመምረጥ እንዲያስተዳድር ይሁንታውን በመስጠቱ የኢህአዴግ አባላትንና ደጋፊዎቹን እንዲሁም መላ የአገራችን ህዝቦች እንኳን ደስ አለን እያለ ህዝቡ የጣለበትን አመኔታ በሙሉ አቅሙ ለመፈፀም በፅናት እንደሚንቀሳቀስ ቃል ገብቷል።

ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ኢህአዴግ ባለፉት አመታት ሲያደርገው እንደነበረው ሁሉ ከህዝቡ ጋር በመሆን በልማቱም ሆነ በዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ መስክ እስካሁን የተገኙትን ውጤቶች በመጠበቅና በማስፋት ያሉትን ችግሮች ደግሞ በማቃለል ረገድ የላቀ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተስማምቷል።

በአሁኑ ወቅት ጎልተው የሚታዩትን የኑሮ ውድነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከህዝቡ ጋር እየተመካከረ በየደረጃውም ቀጥተኛ ተሳትፎውን እያረጋገጠ መፍታት የሚችልበትን አኳኋን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ትኩረት ሰጥቶ መክሯል።

በዚህ አጋጣሚም ህዝቡ የሚፈጠረውን አመቺ ሁኔታ በመጠቀም እንደትናንቱ ሁሉ ከኢህአዴግና ከመንግስት ጎን በመቆም በየአካባቢው የሚታዩ ችግሮችን ለማቃለል የልማትና መልካም አስተዳደር ጥረቶቻችንን ለማጠናከር እንዲነሳ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ጥሪ ማቅረቡን ቃል አቀባዩን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።