የአፍሪካ ሚሌኒየም አከባበር በአቡጃ-ናይጀሪያ

ግንቦት 02, 2000 ዓ/ም

ከጌታቸው ወልዩ(ዋኢማ)

ኢትዮጵያ በዘመን አቆጣጠሯ ከሌሎች አገሮች ልዩነት እንዳላት ይታወቃል፡፡ ይህ የዘመን ቀመሯ የጥንታዊነቷና የታሪካዊነቷ ማሳያ በመሆኑ ልዩ መገለጫዋ ነው፡፡ እንደሚታወቀው አንድ የኢትዮጵያ ዓመት 365 ቀናት ከስድስት ሠዓታት ከ15 ዲግሪ ኬክሮስን ይይዛል፡፡ ከጳጉሜን በቀር ሁሉም ወራት ባለሠላሳ ቀናት ናቸው፡፡ አቆጣጠሩ መሠረት የሚያደርገው ዑደተ -ፀሐይን ሲሆን፤ ባለ ዐራት ወቅት ነው፡፡

በዚህም መሠረት ሀገራችን አዲሱን ሚሌኒየም/ዕሥራ ምእት/ አምና በግንቦት ማብቂያ "ሁለት ዛፍ ለሁለት ሺህ" በሚል ጉልህ መሪ ቃል ማክበሯን ጀምራለች፡፡ በመቀጠልም መስከረም 1/2000 ዓ.ም በሀገር ውስጥና በውጭ አገሮች በታላቅ ድምቀት በሠላምና በስኬት አክብራለች፡፡

አምባሳደር ሱሌማን በናይጄርያ የኢትዮጵያ አምባሳደር

በተለይ የሦስተኛው ሺህ ዓመት ጅማሬ ሚሌኒየም ዓመቱን ሙሉ የሚከበር ከመሆኑ አኳያና ጥር 21 እና 22/1999 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደው ስምንተኛው የአፍሪካ ኅብረት መሪዎች ጉባኤ ላይ የተሳተፉ አፍሪካውያን መሪዎች የኢትዮጵያን ሚሌኒየም የራሳቸው በማድረግ "የአፍሪካ ሚሌኒየም" ተብሎ እንዲከበር በመወሰናቸው የአፍሪካዊነት ባሕሪ ይዟል፡፡

በዚሁ የአህጉሪቱ ርዕሰ ብሔሮች፣ የመንግሥታት መሪዎች፣ የመሪዎችና የሀገር ተወካዮች፣ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ ባንኪ ሙን፣ የዓለም-አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮችና ታዋቂ ግለሰቦች በተገኙበት ታሪካዊ ጉባኤ፤ የኢትዮጵያ ሚሌኒየም "የአፍሪካ ሚሌኒየም" መባሉና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እውቅና መስጠቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል ሆኗል፡፡

በይበልጥም ውሳኔው የነፃነትና የሉዓላዊነት ተምሳሌት የሆነችውን ኢትዮጵያ የረዥም ዘመን ታሪክና ለአፍሪካ አኅጉር ያደረገችውን አስተዋፅኦ በማገናዘብ የተወሰነ በመሆኑ፤ የአገሪቱን ቀደምት ታሪክ የሚያጎላው ነው፡፡ እንዲሁም መሪዎቹ ለኢትዮጵያ፣ ለሕዝቦቿና ለመንግሥቷ ያላቸውን ክብር ያሳዩበት በመሆኑ በደማቅ ታሪክ ተመዝግቧል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ኢትዮጵያ ቀዳሚ የሊግ ኦፍ ኔሽንና የተባበሩት መንግሥታት አባል አገር መሆኗንና፤ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅትና ለአፍሪካ ኅብረት መመስረት እና ለአኅጉሩ ሰላም መስፈን ያደረገችው አስተዋፅኦ ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች ምሳሌ መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡ ስለሆነም ውሳኔው የአፍሪካውያንን እርስበርስ ትብብር፣ ወዳጅነታቸውንና አንድነታቸውን የሚያጠናክር እና መቀራረባቸውን በግልፅ ያሳዩበት የዕውነት መድረክ ሆኗል፡፡ የእነዚህ ሁሉ ድምር ሚሌኒየሙ አኅጉራዊና ዓለም-አቀፋዊ ገፅታ ኖሮት እንዲከበር ኢትዮጵያ ያላትን ፅኑ ፍላጎት ያሳካችበት ነው፡፡

ስለዚህ የአፍሪካ ሚሌኒየም ኢትዮጵያ የረዥም ዘመን ታሪክ ባለቤትነቷን፣ የሰው ልጅ ቀደምት መገኛ እና ብሔር-ብሔረሰቦች ተፋቅረው የሚኖሩባት አገር መሆኗን፣ በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ መመሥረቷን፣ እንግዳ ተቀባይነቷንና ለልማት አመቺነቷን በማሳወቅ፤ መልካም ስሟን ተንተርሶ በርካታ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ዜጎች አገሪቱን የሚጎበኙበት መልካም አጋጣሚ መፍጠር ላይ ያነጣጠረ ዓላማ ይዞ ተነስቷል፡፡

በተጓዳኙ ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ትውልድ ኢትዮጵያውያን እና ሌሎች የኢትዮጵያ ወዳጆች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት፣ ንግድ፣ ቱሪዝም፣ ባህልና በልዩ ልዩ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ መስኮች መዋዕለ-ንዋያቸውን በማፍሰስ ተጠቃሚ ሆነው በልማት አጋዥ ሚና እንዲኖራቸው ማድረግም የሚጠቀስ ነው፡፡

የአፍሪካ መንግሥታትና ሕዝቦቻቸው በዓሉ የራሳቸው በመሆኑ በየአገሮቻቸውና በኢትዮጵያ ውስጥ በመተሳሰብ፣ በአንድነትና በፍቅር በማክበር፣ ለልማት፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ ለመልካም አስተዳደር መረጋገጥ፣ ለዕድገትና ብልፅግና እንዲነሳሱ ምቹ ሁኔታን መፍጠርም የሚሌኒየሙ አከባበር ማዕከል አድርጓል፡፡

ዓላማዎቹን መሠረት በማድረግ ኢትዮጵያውያን፣ የኢትዮጵያ አጋሮችና ወዳጆች ሚሌኒየሙ የአፍሪካ ሚሌኒየም መሆኑን ተረድተው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የሕዝቦችንና ትስስር አጠናክረው ኢትዮጵያ በፖለቲካዊ ሕይወትና በሶሾዮ-ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ በስላ መልካም አስተዳደር የሰፈነባት፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የገነባችና በልማቷ የበለፀገች የማድረግ ግብ አለው፡፡

ሚሌኒየሙ ለአፍሪካ መንግሥታት የአዲስ ሕይወት መሸጋገሪያ በመሆኑ አፍሪካውያን በወንድማማችነትና እህትማማችነት ስሜት በጋራ ተነሳስተው የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝን በመታገል ፤ የበለፀገችና የዳበረች አፍሪካን ለመመስረት ቆርጠው እንዲነሱና የአፍሪካን ሕዳሴ እንዲያረጋግጡ ማድረግ የግቡ አካል ነው፡፡

ከዚህ አኳያ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ከውጭ ጉዳይና ማስታወቂያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚሌኒየምን አከባበር ጽሕፈት ቤት እና ሬዲዮ ፋና ጋ በመተባበር በተያዘው ዓመት የአፍሪካ ሚሌኒየም በናይጀሪያ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ ሱዳንና ጅቡቲ በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ቀዳሚውን ዝግጅትም ሚያዝያ 16/2000 ዓ.ም በናይጀሪያ ዋና ከተማ አቡጃ በድምቀት አክብሯል፡፡

አቡጃው የአፍሪካ ሚሌኒየም በዓል "ከኢትዮ-ናይጀሪያ ቢዝነስ ፎረም" ዝግጅት ጋር ተያይዞ የተካሄደ በመሆኑ ትልቅ ትኩረት ስቦ ነበር፡፡ በበዓሉ ላይ ኢትዮጵያ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ከዲፕሎማቶች፣ ከሚዲያ፣ ከሙዚቃ ባለሙያዎች፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ከሙገር ሲሚንቶ ኢንተርፕራይዝ፣ ከኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን፣ ከኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እና ከአዘጋጆቹ የተወከሉ ሰላሳ የልዑካን ቡድን አባላቷን አሳትፋለች፡፡

የፎረሙ ተሳታፊዎች

በአቡጃ ሼራተን ሆቴል በተካሄደው ዝግጅት ናይጀሪያም በተመሣሣይ ከንግድና ውጭ ጉዳይ፣ ኢንቨስትመንት፣ ባህልና ቱሪዝም መሥሪያ ቤቶች፣ ከግዛቶቿ ተወካዮች፣ ከንግዱ ማኅበረሰብ፣ ከታዋቂ ባለሀብቶች፣ ከምሁራንና ከዕውቅ ሰዎች የተወከሉ አያሌ ተሳታፊዎችን አካፍላለች፡፡ የአፍሪካ ኅብረት በበኩሉ የአፍሪካ ኅብረት አዲስ አጋርነት (ኔፓድ) ተወካዩን በመወከል መድረኩን አስመርቷል፡፡

በበዓሉ ላይም በኢትዮጵያ ሚሌኒየም መነሻነት የአፍሪካ ሚሌኒየም አከባበር፣ የኢትዮጵያ የንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ የመሠረተ ልማትና አጠቃላይ የኢኮኖሚ ገፅታና የፐብሊክ፣ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ዲፕሎማሲ ሁኔታ ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሑፎች በኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ቀርቧል፡፡

ከጥናት አቅራቢያዎቹ መካከል ዶክተር አድኃና ኃይሌ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ የኢትዮጵያን ጥንታዊነት፣ ታሪካዊነት፣ የሰው ዘር ምንጭነትና የሚሌኒየሙን መነሻና አሁን ያለበት ሁኔታ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ባቀረቡት ገለፃም ኢትዮጵያ በረዥም ጊዜ ሥልጣኔዋና ታሪካዊ ሀገርነቷ የውጭ ወራሪዎችን ስትከላከል እንደቆየች ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜም መንግሥት የነፃ ገበያ መርህን በማራመድ በእርሻ መር ኢንዱስትሪ ልማት ትናንሽ አርሶ አደሮችን ወደ ከፍተኛ አርሶ አደርነት ማሻገር ላይ ትኩረት ሠጥቶ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

ዶክተር አድኃና ኃይሌ

ሀገሪቱ የተፋጠነ ልማትን ለማምጣት በምታደርገው ጥረትም ባለፉት አምስት ዓመታት ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገቧንና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እየተረባረበች እንደምትገኝ ዶ/ር አድኃና በማብራሪያቸው ያተኮሩባቸው ጉዳዮች ነበሩ፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ ያለፈችበት ታሪኳን በሚሌኒየሟ በማክበር ላይ ትገኛለች፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵያ ሚሌኒየም የኢትዮጵያ ሕዳሴ እንደሚሆንና በአፍሪካ ሚሌኒየም ደግሞ የአፍሪካን ሕዳሴ ለማረጋገጥ ሀገሪቱ አዲስ ምዕራፍ መጀመሯን አብራርተዋል፡፡

አቶ አቢ ወልደመስቀል የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ባቀረቡት ጥናት ደግሞ፤ ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ አድጓል፡፡ በዚህም ዓመታዊ አጠቃላይ ገቢዋ ከፍ ብሏል፡፡ የውጭ ቀጥታ ኢኮኖሚዋም በስፋት መጨመሩም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ዕድገት መገለጫ ነው፡፡ ለዚህም እንደማሳያ የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ለውጭ ባለሀብቶች በቅድመና ድኅረ-ኢንቨስትመንት አገልግሎት አሰጣጥ የወሰዳቸው ማሻሻያዎች ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኤጀንሲው የኢንቨስትመንት ፈቃድ፣ የንግድ ምዝገባና የቢዝነስ ፈቃድ እያንዳንዳቸው በአራት ሰዓታት ውስጥ ይጠናቀቃሉ፡፡ የሥራ ፈቃድ ደግሞ በአንድ ሰዓት ውስጥ ማለቁ ከማሻሻያው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

አቶ አቢ ወልደመስቀል

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ-ነዋይ ለማፍሰስ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉት የማክሮ ኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና ሶሻል ሁኔታዎች መረጋጋት በአመቺነታቸው ቅድሚያ ይጠቀሳሉ፡፡ ከእነዚህ ጋር በመያያዝ ቀላል የኢንቨስትመንት አሰራሮች እና ርካሽና የሰለጠነ የሰው ኃይል መኖራቸው ለአመቺነቱ ጥሩ ማሳያዎች ናቸው፡፡ በተለይም የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎቹ ከአፍሪካ ዝቅተኛ ወንጀል በሚፈፀምባትና ሙስናን በመዋጋት ረገድ የመንግሥት ቁርጠኝነት በሚታይባት ኢትዮጵያ ውስጥ የውጭ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት በስፋት ቢሳተፉ ተጠቃሚነታቸው ከፍተኛ ነው ይላሉ- አቶ አቢ፡፡

አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ በናይጀሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር በበኩላቸው የኢትዮጵያ ሚሌኒየም የአፍሪካ ሚሌኒየም ሆኖ መከበሩ በአፍሪካ ሕዝቦች መካከል ያለውን አንድነትና የሕዝቦች ግንኙነት በማጠናከር ታላቅ ታሪካዊ ፋይዳን አለው ይላሉ፡፡

በተለይም ኢትዮጵያ ታሪኳንና ገፅታዋን ለዓለም ማኅበረሰብ የምታስተዋውቅበት መድረክ ይሆናል፡፡ ምንም እንኳ አንዳንድ የምዕራባዊያን ሚዲያዎች ኢትዮጵያን ከድርቅና ረሀብ ጋር እያስተሳሰሩ ቢያቀርቡም ሀገራችን የራሷ የዘመን አቆጣጠርና ፊደሎች ያሏት ጥንታዊ ሀገር መሆኗ ሐቅ ነው፡፡ በገሀድም የተረጋገጠ ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ብሔር-ብሔረሰቦች ተፋቅረው የሚኖሩባት፣ የተለያዩ ባሕሎች፣ ወጎች፣ ልማዶችና እሴቶችን ያቀፈች የአንድነትና የፍቅር አገር መሆኗን አምባሳደር ሱሌይማን በገለፃቸው በስፋት አብራርተዋል፡፡

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ስሟ በቅዱስ መጽሐፍና ቁራን በተደጋጋሚ የተገለፀ፣ የሀይማኖት መቻቻልና መከባበር ያለባት፣ በቅኝ ግዛት ያልተያዘች፣ በመካከለኛና ረዥም ርቀት ሩጫ አትሌቶቿ በዓለም የነገሱበት፣ ጥንታዊና ታሪካዊ አገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ ስምንት ያህል ቅርሶቿን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሣይንስና ባሕል ድርጅት "ዩኔስኮ" ያስመዘገበችና ቡናን ለዓለም ያሳወቀችና ያበረከተች በመሆኗም ዓለም ያደንቃታል፡፡

በመሆኑም የእነዚህና ሌሎች መገለጫዎች ያሏት አገር የጥበብ ምድር፣ አንድነትና የሚቻቻሉ ሕዝቦች ባላት ናይጀሪያ የአፍሪካ ሚሌኒየምን በማክበሯ ታላቅ ኩራት እንደሚሰማት እሙን ነው፡፡ ይህ ደግሞ በኢትዮጵያና ናይጀሪያ መካከል ያለውን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት አጠናክሮ በቀጣይ ሀገራቱ በንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች በጋራ እንዲሰሩ እና የአፍሪካን ሚሌኒየም ሕዳሴ ለማረጋገጥ እንዲጥሩ እንደሚያደርጋቸው አያጠራጥርም፡፡

የአፍሪካ ሚሌኒየም በዓልና የኢትዮ-ናይጀሪያ ቢዝነስ ፎረም ሲከበር መድረኩን የመሩት የአፍሪካ ጠረጴዛ ዙሪያ ቢዝነስ ውይይትና የኔፓድ ቢዝነስ ሊቀመንበር ዶክተር ባማንጋ ትኩር በበኩላቸው ያረጋገጡት እውነታ ቢኖር፤ የኢትዮጵያ ሚሌኒየም የአፍሪካ ሚሌኒየም ሆኖ መከበሩ አፍሪካውያን ለኢኮኖሚ ዕድገታቸው ለሚያደርጉት ጥረት ስንቃቸው ሆኖ የሚያገለግል ነው፡፡

ዶክተር ባማንጋ ትኩር

በተለይ ኢትዮጵያ ለየትኛውም ወራሪ ኃይል ሳትንበረከክ የሕዝቦቿን ሉዓላዊነቷን አስከብራ መቆየቷ ልዩ መገለጫዋ ነው፡፡ አሁንም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ያበረከተችው ሚሌኒየም አፍሪካውያን በተሻለ ሁኔታ ትስስራቸውን ይበልጥ አጠናክረው የሚጓዙበት አዲስ ምዕራፍ ነው፡፡ ቀደም ሲልም ኢትዮጵያና የናይጀሪያ ትከሻ ለትከሻ በመደጋገፍ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታና ወደ አፍሪካ ኅብረት ማሻጋገር፣ በፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ያላቸውን የጋራ ጥረት በቀጣይም በንግድና ኢንቨስትመንት ሊደግሙት እንደሚገባ ዶክተር ትኩር ጥሪያቸውን ያቀረቡበት ሁኔታ አለ፡፡

በበዓሉ ላይ ከጥናታዊ ፅሑፎቹ በተጨማሪ የኢትዮጵያን ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርሦች፣ የቱሪስት መስሕቦች፣ የኢትዮጵያን የብሔር-ብሔረሰቦች ሙዚየምነት የሚያሳዩና አሁን ያለውን የልማት እንቅስቃሴ የሚያመላክቱ ዶክመንተሪ ፊልም እና የፎቶግራፍና የሥዕል ዓውደ-ርዕይ በዝግጅቱ ላይ ቀርበው በበዓሉ ተሳታፊዎች ከፍተኛ አድናቆት አትርፈዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችውን ቡና ከቡና አፈላል ሥርዓት ጋር ተዋውቆ ናይጀሪያውያንን ማርኳል፡፡ በኢትዮጵያ የባህል ምግብ እራት የታጀበውና በምሽት የቀረበው የኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃ ትርዒትም በአቡጃ ተቀማጭ የሆኑ ዲፕሎማቶችና አያሌ ጥሪ የተደረገላቸው ዲፕሎማቶችን ቀልብ ስቦ አስጨፍሯል፡፡ ታዳሚዎችን አስደምሟል፡፡ ሀገራችንንም የባህል ማኅደር አሰኝቷል፡፡ በተመሳሳይ የናይጀሪያ የሙዚቃ ቡድንም ልዩ ልዩ የሙዚቃ ትርዒቶችን አቅርቦ በዓሉን አድምቋል፡፡

በናይጀሪያ የኢትዮጵያ ኤምባሲም ዝግጅቱን በማስተባበር፣ ወጪዎችን በመሸፈንና በማስሸፈን፣ የኢትዮጵያን የልዑካን ቡድን በክብር በመቀበል፣ ትራንስፖርት በማመቻቸት፣ አስተባባሪዎችን በአቡጃና በሌጎስ በመመደብ በዓሉን በመምራትና ከተማውን በማስጎብኘት በታሪክ ፊት የሚዘከር ትልቅና ጉልህ ሥራ ሰርቷል፡፡

ነዋሪነታቸው በአቡጃ የሆነና ከአርባና ሃምሳ የማይበልጡ የኢትዮጵያውያ ኮሚኒቲ አባላት የኢትዮጵያን የልዑካን ቡድን በክብር በመቀበል፣ በልዩ ዝግጅቱ ላይ በመሳተፍና የእራት ግብዣ በማድረግ፤ የኢትዮጵያውያን እንግዳ ወዳድነትና ፍቅራቸውን በአክብሮት ገልፀዋል፡፡ የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን አባላትም የአቡጃ ከተማንና የኢትዮጵያን ኤምባሲ ጎብኝተዋል፡፡

በአጠቃላይ የናይጀሪያ የአፍሪካ ሚሌኒየም አከባበር ስኬታማና ኢትዮጵያ በዘመናችን ለአፍሪካና አፍሪካውያን ያበረከተችው ቀደምት ስጦታ በመሆኑ ታላቅ ክብር አግኝታበታለች፡፡ የአፍሪካ ሚሌኒየም በቀጣይ በሱዳንን፣ ደቡብ አፍሪካና ጅቡቲ ይካሄዳል፡፡

በዓሉ የአፍሪካ መንግሥታትና ሕዝቦቻቸው በዓሉ የራሳቸው በመሆኑ በየአገሮቻቸውና በኢትዮጵያ ውስጥ በመተሳሰብ፣ በአንድነትና በፍቅር በማክበር፤ ለልማት፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ ለመልካም አስተዳደር መረጋገጥ፣ ለዕድገትና ብልፅግና እንዲነሳሱ ምቹ ሁኔታ መፍጠርና የዳበረች አፍሪካን ለመመስረት ቆርጠው እንዲነሱ በማድረግ ረገድ ያለው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑ እሙን ነው፡፡