አሸባሪው ትሕነግ በአፋር ክልል እያደረሰ ባለው ጥቃት ከ300 ሺሕ በላይ ዜጎች ተፈናቀሉ

ጥር 30/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ትሕነግ በአፋር ክልል እያደረሰ ባለው ጥቃት በርካታ ንፁኃንን በጅምላ ሲጨፈጭፍ ከ300 ሺሕ በላይ ዜጎችን እንዳፈናቀለ የክልሉ መንግሥት አስታወቀ፡፡

የአፋር ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አሕመድ ካሎይታ የአሸባሪው ትሕነግ ታጣቂዎች በአፋር ክልል 6 ወረዳዎች ዘልቀው በመግባት በተደጋጋሚ የከባድ መሳሪያ ጥቃታቸው ሰላማዊ ሰዎችን እየጨፈጨፉ መሆኑን ለዋልታ ተናግረዋል፡፡

ከከፍታማ ቦታዎች ላይ በሽብር ቡድኑ የሚተኮሱ ከባድ መሳሪያዎችን ለማምከን የክልሉ መንግሥት ከፌደራል መንግሥት በተለይም ከአየር ኃይል ጋር በመቀናጀት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

አሸባሪው ያለ የለሌ ኃይሉን በመጠቀም በክልሉ የሚያደርገውን ወረራ የክልሉ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በቅንጅት እየመከቱ እንደሚገኝም ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

ከጦርነት ውጭ ህይወት እንደሌለው በተደጋጋሚ ያሳየው የሽብር ቡድኑ ትሕነግ የመንግሥትን ወደ ትግራይ ክልል ያለመግባት ውሳኔን እንደዕድል በመጠቀም በአፋርና አማራ ክልል ዳግም ወረራ የመፈፀም እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቷል።

በዚህም አሸባሪው ትሕነግ የኢትዮ-ጂቡቲ ዋና መስመርን ለመቁረጥ በአፋር ለወራት ሲያደርግ የነበረውን ሙከራ አሁን ላይ በድጋሜ እየሞከረ ይገኛል።