ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ ዲያስፖራዎች 22 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ተገማች ገቢ ተገኘ

ጥር 30/2014 (ዋልታ) የመንግሥትን ጥሪ ተቀብለው ወደ አገር ቤት ከገቡት ዲያስፖራዎች 22 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የሚገመት የጥሬ ገንዘብና የዓይነት ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እንድሪስ (ዶ/ር) ዲያስፖራዎቹ ለአገር ከፍተኛ ገቢ ከማስገኘታቸው ባለፈ ለሰላምና ገፅታ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ጠቁመዋል፡፡
የአገር ገፅታ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲገነባ አንዲሁም የአገርን ሃብት በአግባቡ ለመጠቀም እና መዋዕለንዋይ ፈሰስ ለማድረግ ከ400 በላይ ዲያስፖራዎች መመዝገባቸውንም ገልፀዋል፡፡
አገር በአሸባሪው የትሕነግ ቡድን የተከፈተባትን ጦርነት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የሀሰት መረጃዎችን ሲያሰራጩ የነበሩ የውጭ አገራት መገናኛ ብዙኃንን ለመመከት ዲያስፖራው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱም ተነስቷል፡፡
በአመለወርቅ መኳንንት