2ኛው የዩኤስ አፍሪካ ቢዝነስ ፎረም በኒውዮርክ ተካሄደ

በፎረሙ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ከ50 በላይ የአገሮች መሪዎች እንዲሁም 150 ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ተገኝተዋል።

ቢዝነስ ፎረም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም፥ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዷን ለማሳካት በለውጥ ሂደት ውስጥ መሆኗን አስረድተዋል።

በአገሪቷ እየተገነቡ ያሉና ስራ የጀመሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው ሽግግር ጥሩ መንገድ እየፈጠሩ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር እንዲሁም የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱን ለማሳካት ጉልህ ሚና እንዳላቸው አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት 13 ዓመታት ባለሁለት አሃዝ እድገት ማስመዝገቧን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይሄው እድገት ቀጣይነት እንዲኖረው ሁሉን አቀፍ የልማት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ በበኩላቸው፥ አሜሪካ የአፍሪካ ሁለንተናዊ አጋርነት ያስፈልጋታል፤ አሁን ያለው ግንኙነትም ይበልጥ እንዲጠናከር ትሻለች ብለዋል።

በሁለቱም ወገን ያለው የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት እያደገ መምጣቱንም ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት ከ300 በላይ የአሜሪካ ኩባንያዎች በአፍሪካ የንግድ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመው፤ ከ70 በመቶ የሚሆኑ አሜሪካዊያን ባለሃብቶች በአህጉሪቷ ኢንቨስት በማድረግ ላይ መሆናቸውንም አውስተዋል።

የአሜሪካ አፍሪካ ንግድና ቢዝነስ ፎረም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2014 የተጀመረ ሲሆን፥ አሜሪካና አፍሪካ የቢዝነስ ግንኙነት ለማጠናከር ያለመነው። 

ፎረሙ የአሜሪካ ባለሀብቶች በአፍሪካ በኢንቨስትመንት፣ በመሰረተ ልማት፣ በኤልትሪክ ሃይልና በኢነርጂ አቅርቦት፣ በግብርና፣ በጤና ዘርፎች መሳተፍ በሚችሉበት ነጥቦች ላይ የሚያተኩር ነው።

ፎረሙ በተካሄደበት ወቅትም አሜሪካ በአፍሪካ የ33 ቢሊየን ዶላር የኢንቨስትመንት ልማት በአህጉሪቷ ለማከናወን ቃል መግባቷ አይዘነጋም።

በሁለተኛው ፎረምም የንግድና ኢንቨስትመንት ምጣኔ ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተደርጓል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ኬንያ፣ጋና እና ሌሎች የአፍሪካ አገሮችን በጎበኙበት ወቅት አፍሪካ በፈጣን እድገት ውስጥ መሆኗን እንዳረጋገጡም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

በቀጣዮቹ 10 ዓመታት አፍሪካ ፈጣን እድገትና ሁለንተናዊ ለውጥ የማስመዝገብ ሰፊ እድል እንዳላትም አስረድተዋል(ኢዜአ)።