አስተዳደሩ የነዳጅ እጥረት በፈጠሩ የነዳጅ አቅራቢ ተቋማትና ዴፖዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች አፋጣኝ የማጣራት ስራ በመስራት የነዳጅ እጥረት በፈጠሩ የነዳጅ አቅራቢ ተቋማት እና ዴፖዎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ገለጹ፡፡

ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ከንግድ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ሰሞኑን በተፈጠረው የነዳጅ እጥረት ዙሪያ ከማደያ ባለቤቶችና ከነዳጅ አቅራቢ ተቋማት ጋር ባደረጉት ምክክር የተፈጠረው የነዳጅ እጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ባለመወጣታቸው የተፈጠረ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ዘርፉ የረጅም ግዜ መፍትሄ የሚሹ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚንስቴር እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን ያካተተ ግብረ-ሃይል በማቋቋም ገበያውን በቋሚነት የማረጋጋት ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

በመጨረሻም የከተማ አስተዳደሩ ከፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመሆን በከተማዋ ውስጥ ያሉትን የነዳጅ ማደያ ዴፖዎችን የመፈተሽ ስራ ከዛሬ ጀምሮ የሚሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በማከማቻ ነዳጅ እያለ የነዳጅ እጥረት የተፈጠረ በማስመሠል ህብረተሰቡን በማጉላላት የተዛባ ገበያ በመፍጠር ችግር እየፈጠሩ ያሉ ማደያዎች እና የነዳጅ አቅራቢ ተቋማት ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድም ምክትል ከንቲባው አስታውቀዋል፡፡ (ምንጭ፡-የከንቲባ ጽህፈት ቤት)