ኮሚሽኑ የከተማ መሬትን ለግል ጥቅማቸው አውለዋል ተብለው በተጠረጠሩ ሰዎች ላይ ምርመራ ጀመረ

ሀዋሳ 14 /2004/ዋኢማ/ – በደቡብ ክልል ከከተማ መሬት ጋር በተያያዘ በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩ ሠራተኞች እና ሃላፊዎች ላይ የምርመራ ሥራ መጀመሩን የክልሉ ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ ፡፡

የኮሚሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መለስ ዓለሙ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት የምርመራ ሥራው በመካሄድ ላይ የሚገኘው ከከተማ መሬትና ከብድር አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር እና የኦሞ ማይክሮ ፍይናንስ ሠራተኞች እና የሥራ ሃላፊዎች ላይ ነው፡፡

በተለይም በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከሕግ እና ሥርዓት ውጪ የከተማ መሬቶችን በመሸንሸን ያልተገባ ጥቅም በማግኘት የተጠረጠሩ በርካታ ሠራተኞችና የሥራ ሃላፊዎች በቁጥጥር ሥር ውለው በኮሚሽኑ የምርመራ ሥራ እየተካሄደባቸው እንደሚገኝ ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

ሠራተኞቹና የሥራ ሃላፊዎቹ በከተሞች ወጥ የሆነ የመሬት መረጃ ሥርዓት እስኪዘረጋ ድረስ ላልተወሰነ ጊዜ በክልሉ ካቢኔ የተላለፈውን  የከተማ ቦታ ምሪት እገዳን በመጣስ  በጥቅም በመተሳሰር የመንግሥት እና የሕዝብ መሬትን ለግል ጥቅም ማዋላቸውን ዋና ዳይሬክተሩ  አስረድተዋል፡፡

እስከ አሁን በተደረገው የማጣራት ሥራ የምሪት እገዳው ከተላለፈ በሃላ በማዘጋጃ ቤቱ የመረጃ ቋት ውስጥ ያልነበሩ 461 አዳዲስ ቦታዎች በተለያዩ ግለሰቦች እጅ መገኘታቸውን ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል ፡፡

ከመሬት ምሪት በተጨማሪም በኦሞ ማይክሮ ፍይናንስ ተቋም በማገልገል ላይ የነበሩ 34 ሠራተኞች እና የሥራ ሃላፊዎች በተቋሙ ለጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት የሚሰጠውን የብድር አገልግሎት በማስታከክ በርካታ የሙስና ድርጊቶች መፈጸማቸውን ገልጸዋል፡፡

ሠራተኞቹና ሃላፊዎቹ ከተለያዩ ግለሰቦች ጋር በመመሳጠር ሀሰተኛ የጥቃቅን ማህበራትን በማቋቋም የሕገ ወጥ ጥቅም ተካፋይ ከመሆናቸውም በላይ ከተለያዩ አካላት ጋር በመደራደር ያለ ዋስትና ብድሮችን በመስጠት የተቋሙን ጥቅም ማሳጣታቸውን አመልክተዋል፡፡

ኮሚሽኑ በተቋሙ ሠራተኞችና ሃላፊዎች ላይ ምርመራ በጀመረ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ብቻ ተመዝብሮ የቆየና በተለያዩ ግለሰቦች እጅ የነበረ ከ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ለተቋሙ ተመላሽ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ ከከተማ መሬት ጋር በተያያዘ በመሬት ዝርፊያ ላይ የተሠማሩ ሠራተኞችን እና የሥራ ሃላፊዎችን በሕግ የመጠየቁ ጉዳይ ከሀዋሳ ከተማ ውጪ በሚገኙ ሌሎች ከተሞችም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዋና ዳይሬክተሩ  አረጋግጠዋል፡፡

የክልሉ ሕብረተሰብ አገሪቱን ከድህነት ለማላቀቅ የተጀመረው የዕድገት እና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በሙስና እንዳይደናቀፍ ከኮሚሽኑ ጎን በመቆም የሕዝብ እና የመንግሥት መሬቶችን የዘረፉ ግለሰቦችን በማጋለጥ እና መረጃዎችን በመስጠት የዜግነት ሃላፊነቱን እንዲወጣ ዋና ዳይሬክተር ጥሪ አቅርበዋል፡፡