የታላቁን ህዳሴ ግድብ ተጽዕኖ ለመገምገም ካይሮ ላይ ስብሰባ ተካሄደ

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 16 2004 /ዋኢማ / – የታላቁ ህዳሴ ግድብ በታችኛዉ የተፋሰስ አገሮቸ ላይ ሊኖረዉ የሚችለዉን ተፅዕኖ ለመገምገም የኢትዮጵያ፣ የሱዳን እና የግብፅ ኤክስፐርቶችን ያሳተፈ ስብሰባ ግብፅ ካይሮ ላይ ተካሄደ።

ስብሰባዉ ሦስቱ አገሮች ባሳለፍነዉ ህደር ወር መጨረሻ ግብፅ ላይ በደረሱት ስምምነት መሰረት የተካሄደ ነዉ።

በስምምነቱ መሰረት በኮሚቴዉ ሦስቱንም አገራት የሚወክሉ ስድስት ባለሙያዎች እና አራት ተጨማሪ የዉጭ ባለሙያዎች ይካተታሉ።

በኢትዮጵያ የግብፅ አምባሳደር ሞሐሙድ ፋቲ እንደተናገሩት ለሦስት ቀን የሚካሄደዉ ስብሰባ የህዳሴዉን ግድብ አስመልክቶ ሦስቱ አገሮች የደረሱበትን ስምምነት ያጠናክራል፤ በሦስቱ አገሮች የተጀመረዉን የሦስትዮሽ ትብብርም ወደተሻለ ደረጃ ያሸጋግራል።

በተመሳሳይ የግብፁ ጠቅላይ ሚኒስትር ካማል ኤል-ጋንዙሪ የአባይ ተፋሰስን አስመልክቶ ከሱዳን የዉሃ ሃብት እና መስኖ ሚኒስትር ሰይፈዲን ሐማድ ጋር በወቅታዊ ጉዳዩች ዙሪያ ትናንት ተወያይተዋል።

በግብፅ እና በሱዳን የዉሃ ሃብት ሚኒስትሮች መካከል ያለዉን ትብብር ማጠናከር ፣የቴክኒክና የሥልጠና ድጋፍ እንድሁም በአባይ ተፋሰስ አገሮች መካከል በተደረሱ ስምምነቶች ለይ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ባለስለጣናቱ የተወያዩባቸዉ ርዕሰ ጉዳዮች ናቸዉ።

የሱዳን የዉሃ ሃብት እና መስኖ ሚኒስትር ሰይፈዲን ሐማድ ከዉይይቱ በኃላ እንደተናገሩት ሁለቱ አገሮች በዓባይ ጉዳይ ላይ ከዚህ ቀደም የነበሩትን ልዩነቶች በማጥበብ ከታችኛዉም ሆነ ከላይኛዉ ተፋሰስ አገሮች ጋር አዲስ የትብብር ምዕራፍ ለመጀመር የጋራ ራዕይ አላቸዉ።

ሚኒስትሩ አክለዉም ኢትዮጵያ በመገንባት ላይ ያለችዉ ግድብም ሆነ ሌሎች በዓባይ ላይ የሚካሄዱ ፕሮጄክቶች በአገራቱ ትብብር እና ስምምነት ከተካሄዱ ብዙ ጥቅም እንዳላቸዉ መናገራቸዉን የዘገበዉ የግብፅ የመረጃ አገልግሎት ነዉ።