የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ታህሳስ 10 ቀን 2004 ዓ.ም መደነኛ ስብሰባውን ያክሂዳል

 

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 9/2004 (ዋኢማ) – የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ታህሳስ 10 ቀን 2004 ዓ.ም መደበኛ ስብሰባውን እንደሚያካሂድ አስታወቀ፡፡

ባለፈው ዓመት በእንዱስትሪ ልማት መስክ የነበሩ አፈጻጸሞችንና የታዩ አዝማሚያዎችን በዝርዝር ይመረምራል ተብሎ እንደሚታመንም ከኢህአዴግ ጽ/ቤት የደረሰን መግላጫ ያሳያል፡፡

ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በተለይ የአምስት ዓመቱን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ መንግሥት አጠቃላይ ልማቱን ወደፊት ለማራመድ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ረገድ ለሚታዩ ችግሮች የመፍትሄ አቅጣጫ ያስቀምጣል፡፡

እንዲሁም በግል ባለሃብቱ ሊሰሩ የማይችሉትንና ለአጠቃላይ ልማቱ አስፈላጊ የሆኑ የልማት ተቋማትን ከማደራጀት አኳያ የተመዘገቡ ውጤቶችንና ያጋጠሙ ችግሮችን በመገምገም የመፍትሄ አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥ ይጠበቃል፡፡

የኢግአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የግል ባለሃብቶች ወደ ልማታዊ አቅጣጫ እንዲያመሩ የተደረጉ እንቅስቃሴዎችንና የተመዘገቡ ውጤቶችንም ይገመግማል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞም የኪራይ ሰብሳቢነት ችግርን ለመቆጣጠር የተወሰዱ እርጃዎችንና የተገኙ ውጤቶችን እንዲሁም ልማታዊ አስተሳሰብን በማጐልበትና የልማታዊ ባለሃብቱን የመወዳደር አቅም በመገንባት ለማጠናከር የሚቻልባቸውን ዝርዝር አቅጣጫዎች ያስቀምጣል፡፡

ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ለዚህ የሚበጁ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ መደበኛ ስብሰባውን ያጠቃልላል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ለዋኢማ  በላከው ዜና አስታውቋል፡፡