ኮሚሸኑ የ27 ሺህ ባለስልጣናትን፣ ተመራጮችና ሰራተኞችን ኃብት መዘገበ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 16 ቀን 2004 (ዋኢማ) – የፌደራሉ የስነ ምግባርና ፀረሙስና ኮሚሸን በእስካሁኑ ሂደት በሐብት ማሳወቅና ምዝገባ የ27 ሺህ የመንግስት ተሿሚ ባለስልጣናትን፣ ተመራጮችንና ሰራተኞችን ሀብትና ንበረት መመዝገቡን አስታወቀ፡፡

ለ4 ሺህ 500 ተመዝጋቢዎችም የምስክር ወረቀት ለመስጠት መዘጋጀቱን ገልጧል፡፡

የኮሚሽኑ የስነ ምግባር ትምህርትና ኮሙዩኒኬሸን ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አሰፋ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዛሬ እንደገለጹት ሐብትና ንብረታቸውን ያስመዘገቡት ከፍተኛ ባለስልጣናትና የመንግስት ሰራተኞች አዋጁ በቀጥታ የሚመለከታቸው ናቸው፡፡

የምዝገባ ሂደቱ ሕዳር 22 ቀን 2003 ዓ/ም መጀመሩን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ እስካሁን ውጤታማ የሚያደርጉ የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

እነዚህን መረጃዎች አደራጅቶ ሕብረተሰቡ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አማካኝነት እንዲያገኛቸው ለማድረግ የሚያስችል ስራም ኮሚሽኑ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በዚህ ረገድ ከውጭ አገር ለጋሾች ጋር ድጋፍ በሚያደርጉበት ሁኔታ ላይ የግኑኝነት ስራ ተከናውኖ ተስፋ መስጠታቸውን ጠቁመው ከኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘም ሕብረተሰቡ መረጃዎቹን እንዴት ማግኘት እንደሚችል ጥናት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የሃብት ማሳወቅና የምዝገባ ስራ በአገሪቱ የመጀመሪያ በመሆኑ እስካሁን ከተገኙ ተሞክሮዎችና የአሰራር ሂደቶች በየጊዜው እየተሻሻሉ መምጣታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ወደፊትም የተሰበሰቡ መረጃዎች በሙሉ በተቻለ መጠን ለህዝብ በቀላሉ እንዲደርሱና እንዲያውቃቸው የማድረጉ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

እስካሁን ከተመዘገቡ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃለፊዎች፣ ተመራጮችና ሰራተኞች መካከል በቅድሚያ ሐብትና ንብረታቸውን አሳውቀው ላስመዘገቡ ከ4 ሺህ 500 ለሚሆኑ ሰዎች ኮሚሽን የምስክር ወረቀት እንዳዘጋጀላቸውም ገልጸዋል፡፡

በምዝገባው ቅደም ተከተል መሰረት የተዘጋጁት የምስክር ወረቀቶች ለእያንዳንዱ ተመዝጋቢ የመስጠት ስራም ኮሚሽኑ በቅርቡ እንደሚጀምርም አስታውቀዋል፡፡ (ኢዜአ)