በደቡብ ክልል የቤተሰብ ምጣኔ አገልገሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር እያደገ ነው

ሀዋሳ ፤ ታህሳስ 17 2004/ዋኢማ/ – በደቡብ ክልል የቤተሰብ ምጣኔ አገልገሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር እያደገ መምጣቱን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ::

በክልሉ ከሁለት ዓመታት በፊት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እናቶች ቁጥር አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን እንደነበረ ያስታወሰዉ ቢሮዉ በተያዘው ዓመት ሁለት ሚሊዮን 129 ሺህ መድረሱን አሰታዉቋል::

በውጤቱም በክልሉ በ 2002 ዓ.ም 57 በመቶ የነበረውን አጠቃላይ የቤተሰብ ምጣኔ አገልገሎት ሽፋን  ወደ 65 በመቶ ለማሳደግ ማስቻሉን  የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ያለው አባተ ገልጸዋል::

በክልሉ የቤተሰብ ምጣኔ አገልገሎት ሽፋን ተጠቃሚዎች ቁጥር ሊጨምር የቻለው ቢሮው በገጠርና በከተሞች የተቀናጀ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ተግባራዊ በማድረጉ መሆኑን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው አስረድተዋል::

ቢሮው በቀጣይ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትን ጨምሮ በመከላከል ላይ ያተኮሩ የጤና ፓኬጆችን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ዕቅድ ነድፎ እየሠራ እንደሚገኝ ባለሙያው  ገልጸዋል::

ዕቅዱን ለማሳካትም በየደረጃው የሚገኙ የጤና አመራሮች እና በገጠርና በከተሞች የተሠማሩ ሰባት ሺህ 353 የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ትኩረት ሰጥተዉ እየሠሩ እንደሚገኙ ባለሙያው አመልክተዋል::

በተጨማሪም ሞዴል የጤና አባዎራዎችን በማቀናጀት ሠፊ የጤና ሠራዊት ለመገንባት ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ከባለሙያው ገለጻ ለመረዳት ትችሏል ::