የሰሜን ጎንደር ዞን ጸጥታ ጉዳዮች መምሪያ ለአካባቢው ሰላም መጠበቅ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገለጸ

 ህብረተሰቡ በተሳሳተ መረጃ ሳይደናገር የአካባቢውን ሰላም ለመጠበቅ ከጸጥታ ሃይሎ ጎን በመሰለፍ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚባ የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደርና ጸጥታ ጉዳዮች መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ሃላፊ አቶ መኳንንት መልካሙ በዞኑ ወቅታዊ ሰላምና ማረጋጋት  ዙሪያ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች በአሁኑ ሰዓት የተረጋጋ ሰላም መኖሩን ገልፀዋል፡፡

ህብረተሰቡ በአሉቧልታ ወሬ ሳይደናገር መንግስት የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በሚያደርገው ጥረት የጀመረውን ድጋፍና ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

በዞኑ የተፈጠረውን ሰላምና መረጋጋት ለማደፍረስ ''መንግስት ትጥቅ እያስፈታ ነው'' በሚል የሚናፈሰው ወሬ ከእውነት የራቀ መሆኑን በመገንዘብ አጥብቆ ሊቃወመው እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

“መንግስት ትጥቅ የማስፈታት አለማ የለውም’’ ያሉት ኃላፊው ከ2007 ጀምሮና ከዛም በፊት ህጋዊ የጦር መሳሪያ ፈቃድ መሰጠቱን አስታውሰዋል፡፡

''በጦር መሳሪያው እጅ ከፍንጅ ወንጀል ሲፈጽም እስካልተገኘ ድረስ ህጋዊ የጦር መሳሪያ ፈቃድ ያለው ግለሰብ ትጥቅ እንዲፈታ የተደረገበት ሁኔታ የለም'' ብለዋል ሃላፊው፡፡

“በፍርድ ቤት ትእዛዝ ካልሆነና ፖሊስ በጦር መሳሪያ ለተፈጸመ ወንጀል መሳሪያውን በኤግዚቪትነት ለማቅረብ አስገዳጅ ሁኔታ እስካልተፈጠረ ድረስ በማናቸውም ሁኔታ የሰላማዊ ሰዎችን የጦር መሳሪያ ትጥቅ ለማስፈታት አልተሞከረም’’  ብለዋል፡፡

በአንዳንዳድ አካባቢዎች የሚስተዋለውን ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ለመግታት መንግስት ተገቢውን ቁጥጥርና ክትትል እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

ሰሞኑን ''ጅምላ እስር እየተካሄደ ነው'' በሚል የሚናፈሰው ወሬም ከእውነት የራቀ መሆኑን ገልፀው ''የታሰሩት ጥቂት  ግለሰቦችም ቢሆኑ በግርግሩ ወቅት የሰው ሕይወት እንዲጠፋና ንብረት እንዲወድም አድርገዋል በሚል ተጠርጥረው የታሰሩ ናቸው'' ብለዋል፡፡

ማንኛውም ግለሰብ በወንጀል ድርጊት እስካልተሳተፈ ድረስ ስጋት ሊገባው እንደማይገባና አሁን በእስር ላይ የሚገኙትም ቢሆኑ በወንጀል ድርጊቱ እስካልተሳተፉ ድረስ ምርመራው ተጣርቶ ነጻ መሆናቸው ሲረጋገጥ ሊለቀቁ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

ህዝቡ ከምንም በላይ የሰላምን ጠቀሜታ በውል በመገንዘብና ለአፍራሽ ሃይሎች ፕሮፓጋንዳ ጆሮ ሳይሰጥ በአካባቢው የሰፈነው ሰላም እንዲጠናከርና ልማቱም እንዳይደናቀፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ኃላፊው አሳስበዋል/ኢዜአ/፡፡