የውጭ ጉዳይ ፓሊሲው ዓላማ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲን እውን ማድረግ ነው – አቶ ተወልደ ሙሉጌታ

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዋነኛ  ዓላማ  በአገሪቱ ሰላምን፣ ልማትንና ዴሞክራሲን እውን  ማድረግ  መሆኑን  የውጭ  ጉዳይ  ሚንስቴር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ  ገለጹ ።

አቶ ተወልደ ለዋኢማ እንደገለጹት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው በአገሪቱ ዘላቂ  ሰላምና ዴሞክራሲን በማረጋገጥ የአገር ልማትን ሊያግዝ በሚችል መልኩ የውጭ ንግድና ኢንቨስትመንትን  ማስፋፋት  ነው ብለዋል ።

በተለይ  የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ሥራው  ከፍተኛ  ትኩረት  የተሠጠው  መሆኑን  የጠቆሙት አቶ ተወልደ በዓለም የንግድና ኢንቨትመንት ሥራዎች ተዋቂ የሆኑትን ትልልቅ ኩባንያዎችን  በመሳብ ረገድ  የተሠሩ ሥራዎች ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ይናገራሉ ።

ሚኒስቴሩ ግዙፍ ኩባንያዎችንም ሆነ በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን ለመሳብ  የአገሪቷ  ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም  ተከታታይና ፈጣን  የኢኮኖሚ ዕድገት፤ በቂ የሰው ኃይልና ገበያ መኖሩ  ጉልህ አስተዋጽኦ  ማድረጉን   አቶ ተወልደ አስረድተዋል ።

በተጨማሪም አገሪቱ የቀረጸችውና ተግባራዊ ያደረገቺው ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲና ለውጭ ባለሃብቶች  የምትሠጣቸው ማበረታቻዎችም  ባለሃብቶችን ለመሳብ እንዲሁ እገዛ ማድረጉን አቶ ተወልደ አክለው ገልጸዋል ።

በአሁኑ ወቅት በርካታ ዜጎችን ለማሳተፍ የሚያስችሉ፣ አስፈላጊው ግብዓቶችና መሠረተ ልማቶች የተሟሉላቸው   ትላልቅ የኢንዱስትሪ ፓርኮች   በመገንባት ላይ ይገኛሉ ያሉት አቶ ተወልደ ፓርኮቹ አገሪቷ ከተለያዩ የጎረቤት አገራት ጋር በመፎካካር በኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ የተሠማሩ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን ይበልጥ እንዲሠማሩ መልካም እድል እየፈጠረ መሆኑን አመክልክተዋል  ።

በውጭ  የሚገኙ የኢትዮጵያ ኢምባሲዎች በተለይ የኢኮኖሚው ዲፕሎማሲው የተሳካ እንዲሆን  በጥናት ላይ የተመሠረተ  እንቅስቃሴዎችን  እያካሄዱ መሆኑን  ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።