በአዲስ አበባ የሽብር ጥቃት ሊፈጽሙ ሲሉ የተያዙ ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ

በአዲስ አበባ ስታዲየም ቦሌ ፍሬንድ ሺፕ ህንጻ፣ መርካቶና ሌሎች አካባቢዎች ላይ ዜግነታቸው ሶማሊያዊ የሆኑ የሽብር ጥቃት ሊፈጽሙ ሲሉ የተያዙ ግለሰቦች በእስራት መቀጣታቸውን የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ የወንጀል ችሎት አስታወቀ  ።

ተከሳሾች 1ኛ መሐመድ አብዱራሕማን ፣ 2ኛ መሀመድ አህመድ ፣ 3ኛ መሀመድ አብዱላሂ  እና ሌሎች አምስት ተከሳሾችን ጨምሮ ለተከሳሾች ቤት አከራይ የሆኑት 9ኛ እና 10ኛ ተከሳሾችም እንፈደሚገኙበት ገልጿል ።

እነዚህ ተከሳሾች በህገ ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት አዲስ አበባ ቦሌ ሚካኤል አካባቢ ሰላማዊ ዜጋ መስለው የአልሻባብን ተልዕኮ ለመፈጸም  በህቡዕ ተደራጅተው ቤት መከራየታቸው ችሎቱ በክስ መዝገቡ ጠቅሷል።

ከሽብር ቡድኑ በሚሰጣቸው ተልዕኮ መሰረት አዲስ አበባ ላይ የፈንጂ ጥቃት ለማድረስ ህዝብ በብዛት የሚገኝባቸውን አዲስ አበባ ስታዲየም፣ ቦሌ ፍሬንድሽፕ ህንጻ፤ መርካቶና ኤድናሞል የመሳሰሉ ቦታዎችን መርጠው በመለየትና ፎቶ በማንሳት ሲፈጽሙ እንደነበርም  ነው የዘረዘረው ።

በዚህም የህብረተሰቡን ደህንነት ለአደጋ ያጋለጠ ተግባር ፈጽመዋል በማለት አቃቤ ህግ ክስ እንደመሰረተባቸው ነው ያስታወቀው ።

1ኛ ተከሳሽ በሽብር ቡድኑ ተመልምሎ በኢትዮጵያ ለሚደርሱ ጥቃቶች የስራ ክፍፍል የሚሰጥ የሴሉና የፋይናንስ ሀላፊ ጭምር ሆኖ የሚሰራ መሆኑን ገልጿል ።

ግለሰቡ ሶማሊያ ሞቃዲሾ ላይ በተሰጠው ስልጠና አማካኝነት መስከረም ወር 2002 ዓ.ም በህገ ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ቦሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ቦሌ ሚካኤል አካባቢ ቤት ተከራይቶ ይኖር እንደነበርም ነው የአቃቢ ህግ ክስ የሚያስረዳው።

ግለሰቡ በተከራየው ቤት ሙዚቃ ቤት በመክፈትና እንደ ሽፋን በመጠቀም ለሽብር ድርጊት አፈጻጸም ሲጠቀምበት ቆይቷል ነው ያለው ፡፡

ይኸው ተከሳሽ ከሌሎች አጋሮቹ ጋር በመሆን ጥቃት የሚያደርሱበትን ቦታ ለይቶ የአልሻባብ አመራር ለሆነው ወሌ አብዱራህማን ማሳወቁም በክሱ ጠቁሟል።

አመራሩም በተላከለት የፎቶ ማስረጃ አማካኝነት 6 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ለሽብር ማስፈጸሚያነት መላኩን ነው ያረጋገጠው ።

ጥቅምት 3 ቀን 2006 ዓመተ ምህረት በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮጵያ ከናይጄሪያ በሚያደርጉት የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ላይ  በ1ኛ ተከሳሽ አማካኝነት ወደ ሀገር ውስጥ የገቡትን አብዲ እና ሀሰን የተባሉ አጥፍቶ ጠፊዎችን ፈንጂ አስታጥቀው ወደ ስታዲየም ካልሆነም በስታዲየሙ ዙሪያ ፈንጂ በማፈንዳት ጉዳት እንዲያደርሱ  መላካቸውን ገልጿል።

ይሁንና በዕለቱ የነበረውን የጸጥታ ሀይል ፍተሻ ማለፍ ባለመቻላቸው ከቀኑ 7 ሰዓት ከ45 ላይ ለ3ኛ ተከሳሽ ስልክ ደውለው ማለፍ እንዳልቻሉ በመንገራቸው የወደፊት ዕቅዳቸው እንዳይበላሽ  እንዲመለሱ እንዳደረጋቸው ያትታል ክሱ ።

በዕለቱ ምሽት 8 ሰዓት ከ45 ላይ አጥፍቶ ጠፊዎች የታጠቁት ፈንጂ ከጥንቃቄ ጉድለት ፈንድቶ ህይወታቸው ማለፉንም ነው የጠቀሰው

 ።

2ኛ ተከሳሽ የሽብር ቡድኑ አባላትን ጅግጅጋ ከተማ ድረስ በመሄድ ወደ አዲስ አበባ በማምጣት ሲያስተባብር ፤4ኛ ተከሳሽ ደግሞ የፈንጂ ጥቃት እንዴት እንደሚደርስ ለቡድኑ አባላት ስልጠና መስጠቱን ነው የአቃቢ ህግ ክስ የሚያስረዳው።

5ኛ ተከሳሽ ኡስማን መሀመድ ከአባልነቱ በተጨማሪ ህዳር ወር ሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በሚከበረው የብሄር ብሄረሰቦች በዓል ላይ የፈንጂ ጥቃት እንዲደርስ እቅድ በማውጣት ፤ ስለአፈጻጸሙ ሁኔታ ከሽብር ቡድኑ አባላት ጋር በከተማዋ ተዘዋውሮ ጥናት አድርጎ ሪፖርት አቅርቧል ።

እንደ አቃቢ ህግ የክስ ማስረጃ 6ኛ፣ 7ኛ እና 8ኛ ተከሳሾችም በተለያየ ደረጃ በሽብር ቡድኑ ተሳትፎ በማድረግ ለወንጀል ድርጊቱ መሳካት ሲሰሩ ቆይተዋል ነው ያለው ።

ይሁንና ግን ያሰቡትን የወንጀል ድርጊት ሳያሳኩ በጸጥታ ሀይል ክትትልና በህብረተሰቡ ጥቆማ መያዛቸውን አስረድቷል ።

ፍርድ ቤት ቀርበውም የወንጀል ድርጊቱን አልፈጸምንም ሲሉ ክደው የተከራከሩ ሲሆን ፤ አቃቤ ህግ በበኩሉ የወንጀል ድርጊቱን ስለመፈጸማቸው የሚያስረዳ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ ማስመስከሩን ገልጿል ።

በዚሁም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ የወንጀል ችሎት 1ኛ ተከሳሽና የቡዱኑን ዋና መሪ በዘጠኝ አመት ጽኑ እስራት፣ 2ኛ፤ 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾችን እያንዳንዳቸው በስምንት አመት ጽኑ እስራት፣ 6ኛ እና 7ኛ ተከሳሽን በአምስት እና ስድስት አመት ጽኑ እስራት ሲቀጣ፤ 8ኛ ተከሳሽን በሁለት አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን ነው ያስታወቀው ።

እንደዚሁም ችሎቱ 9 እና 10ኛ ተከሳሾች ግን አከራይ እንደመሆናቸው መጠን የውጭ ሀገር ዜጋ ሲከራይ በ24 ሰዓት ውስጥ ማሳወቅ ሲገባቸው ይህን ማድረግ ባለመቻላቸው ጥፋተኛ ብሏል ።

ይሁን እንጅ ተከሳሾች በቀረበባቸው ክስ የሚቀጡት ቅጣት፤በማረሚያ ቤት ከቆዩበት ጊዜ አንጻር አነስተኛ ሆኖ ስለተገኘ በነጻ እንዲሰናበቱ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መስጠቱን ተመለክቷል -(ኤፍ.ቢ.ሲ) ።