የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሁለት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በትላንትናው ዕለት ባካሄደው 61ኛ መደበኛ ስብሰባ በሁለት ረቂቅ አዋጆች ላይ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት አስታውቋል።

ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባው በማዕድን ግብይት ረቂቅ አዋጅ እና በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው የተወያየው፡፡

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ አዋጁ ዜጎች በየደረጃው በሚካሄድ ነፃ፣ ፍትሃዊና ሰላማዊ ምርጫ በማካሄድ በመረጧቸው ተወካዮች አማካኝነት ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ስልጣናቸውን በተግባር እንዲያውሉ ለማድረግ ነፃ የምርጫ አስፈጻሚ አካል አስፈላጊ በመሆኑ እና በኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ለማጠናከር ብሄራዊ ምርጫ ቦርድን ከማንኛውም አካል ነፃ አድርጎ በማደራጀት ፍትሃዊ፣ ተአማኒና ሰላማዊ ምርጫ ለማስፈጸም ይቻል ዘንድ ነው በጠቅላይ አቃቤ ህግ ተዘጋጅቶ የቀረበው።

ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየበት በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል አዋጁን ተቀብሎ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።

ምክር ቤቱ በተጨማሪም በማዕድን ግብይት ረቂቅ አዋጅ ላይም ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

ረቂቅ አዋጁ የሁሉንም አይነት ማዕድን ግብይት ለማስፋፋት፣ ሕጋዊ ስርአት ለማስያዝና፣ ለመቆጣጠር የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ የሚያስፈልግ በመሆኑና የማዕድን ግብይት ስርአትን ዘመናዊ በማድረግ ዘርፉ ለኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ የሚያስችል የግብይት ስርአት ለመፍጠር በማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ ነው ለምክር ቤቱ የቀረበው።

ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ማሻሻያዎችን በማከል ተቀብሎ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ (ምንጭ፡-የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት)