ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ በተባበሩት መንግስታት ጽ/ቤት የአፍሪካ ህብረት ልዩ ተወካይ ጋር መከሩ

ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጽ/ቤት የአፍሪካ ህብረት ልዩ ተወካይን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።

በቅርቡ በተባበሩት መንግስታት ጽህፈት ቤት የአፍሪካ ህብረት ልዩ ተወካይ ሆነው የተሾሙት ሀና ሰርዋ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅን በመተካት የተሰየሙ ሲሆን የጉብኝታቸው ዓላማም ለፕሬዝዳንቷ የእንኳን ደስ አለዎ መልዕክት ለማስተላለፍና ልምዳቸውን ለመካፈል መሆኑን ገልጸዋል።

ቀደም ሲልም በተባበሩት መንግስታት የናይሮቢ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ጄነራል ኃላፊነትን ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴን ተክተው መሥራታቸውንም ተናግረዋል።

ሀና ሰርዋ አክለውም ፕሬዝዳንቷ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአፍሪካ ቢሮና በሌሎች ኃላፊነቶች ላይ የነበራቸውን የመሪነት ሚናም “በጣም ጥሩ” እንደነበር አንስተዋል።

በቀጣይም የተባባሩት መንግስታት ድርጅት ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ጋር የሚሠሩዋቸውን ስራዎች የተሻለ ለማድረግ በመመካከር እንሰራለን ነው ያሉት።

በፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አብርሃም ግርማይ በተባበሩት መንግስታት ጽህፈት ቤት የአፍሪካ ህብረት ልዩ ተወካይ የሆኑት ሀና ሰርዋ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ እንደሚደግፉ መናገራቸውን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም የተባበሩት መንግስታት ከአፍሪካ ጋር በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር መስራት በሚችልባቸው መንገዶች ላይም መወያየታቸውን ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅም በኢትዮጵያ ታሪክ ሴቶች መሪ የመሆን ልምድ መኖሩንና ለሌሎች አገራትም ለአብነት የሚጠቀስ መሆኑን ማንሳታቸውን አክለዋል።(ኢዜአ)