በአማራና ትግራይ ህዝቦች መካከል ግጭትም የግጭት ፍላጎትም የለም- የአማራናትግራይ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች

በአማራና ትግራይ ህዝቦች መካከል ግጭትም የግጭት ፍላጎትም እንደሌለ የአማራና ትግራይ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ገለጹ።

የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በተለያዩ አካባቢዎች ሲያደርጉት የነበረውን የሰላም ጉዞ አስመልክቶ በዛሬው እለት በአዲስ አበባ የማጠቃለያ መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይም ከተለያዩ የሀይማኖት ተቋማት የተውጣጡ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የክልል ርእሳነ መስተዳድሮች ተሳትፈዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ “የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በተለያዩ አካባቢዎች የሰላም አጀንዳ ይዘው በመንቀሳቀሳቸው ሊመሰገኑ ይገባል” ብለዋል።

ምክንያቱ ደግሞ ሰላም ከሁሉም በፊት አንገብጋቢ አጀንዳ በመሆኑ ነው ሲሉም አቶ ገዱ ተናግረዋል።

“ሰላም ለራሳችን፣ ለሀገራችን፣ ለምንመራው ህዝብ፣ ለልጆቻችን አስፈላጊ ነው” ያሉት አቶ ገዱ፥ “ምክንያቱም የሰላም መጥፋት ምን ያክል ጉዳት እንዳለው ስለምናውቅ ነው” ብለዋል።

አቶ ገዱ በመግለጫቸው፥ “የአማራ ክልል ህዝብ ከሁሉም ጋር ሰላም መሆን ይፈልጋል፤ ከህዝቡ ጋር በነበራችሁ ውይይትም ይህንን ማረጋገጥ ችላቹዋል፤ እኔም ለሰላም በቁርጠኝነት ለመስራት ዝግጁ ነኝ” ብለዋል።

“የአማራ ህዝብ እና የትግራይ ህዝብ የጋራ ታሪክ እና እሴት ያለው ህዘብ ነው” ያሉት ርእሰ መስተዳድር አቶ ገዱ፥ አንዱ አንዱን የሚፈራ ሳይሆን አንዱ በአንዱ የሚኮራ ህዝብ ነው ብለዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህ እየተሸረሸረ መምጣቱንም ርእሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በመግለጫቸው አንስተዋል።

የአማራ ህዝብ ከትግራይ ህዝብ ጋር ግጭት አይፈልግም፤ ይልቁንም በመካከላቸው ያለው አለመግባባት ሰላማዊ በሆነ መንገድ እና በውይይት እንዲፈታ ይፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል።

“እኔም የአማራ ህዝብ መሪ እንደመሆኔ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ በቁርጠኝነት እሰራለሁ” ሲሉም አረጋግጠዋል።

የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው፥ የሀይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ሰላምን ለማምጣት ላደረጉት ጥረት ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።

የሀይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች እዚህ ውስጥ በመግባታቸው ሀዘን ተሰምቶኛል፤ ምክንያቱም እኛ ፖለቲከኞች መስራት የነበረንን ባለመነስራታችን ነው እዚህ ውስጥ የገባችሁት ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት እርስ በእርስ ያለው ጥላቻ፣ ፍርጃ፣ ጥቃት እና መፈናቀል በጣም አሳፋሪ ነው፤ ፖለቲካን ትተን በፊት የነበሩ የኢትዮጵያ መሪዎችን ከተመለከትን ከራሳቸው አልፎ ከሌሎች ሀገራት የተፈናቀሉትን በክብር ተቀብለው የማስተናገድ እሴት ነበረን፤ ይህንን እያለን እንዴት እዚህ ውስጥ ገባን ሲሉም ጠይቀዋል።

ከዚህ በፊት ለተፈጠሩ ችግሮች የእከሌ ነው የሚባል ነገር የለም ያሉት ዶክተር ደብረጺዮን፥ ሁለችንም አጥፍተናል፤ ይህንን ለማስተካከልም መረባረብ አለብን ብለዋል።

ከሰላም በላይ ምንም ነገር የለም ያሉት ዶክተር ደብረጺዮን፥ የፖለቲካን ጉዳይ ለብቻ የሰላምን ጉዳይ ለብቻ አድርገን መስራት አለብን ሲሉም ተናግረዋል።

የፖለቲካውን ጉዳይ ለምርጫ በመተው ሁላችንም በሰላሙ ጉዳይ መረባረብ አስፈላጊ መሆኑንም ነው የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል የገለፁት። (ኤፍ.ቢ.ሲ)