የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትን መሥሪያ ቤትን ጎበኘ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትን መሥሪያ ቤትን ጎብኝተዋል፡፡

ተቋሙ በአጭር  ጊዜ  ያከናወናቸውን የሪፎርም ተግባራትን በማስመልከት ለምክር ቤቱ  የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች  ቋሚ ኮሚቴ አባላት ሪፖርት አቅርቧል፡፡

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ኃላፊ ጀነራል አደም መሐመድ ተቋሙ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን ለውጥ መሠረት በማድረግ ስትራቴጂካዊ የለውጥ ዕቅድ በማውጣት የሪፎርም ሥራዎች መሥራቱን ገልጸዋል፡፡

በዚህም  ተቋሙ የአመራሮች ለውጥ ማድረጉንና ሁሉም የተቋሙ ሠራተኛ ከፖለቲካ አመለካከት የፀዳና በህገ-መንግስቱ የተሠጠውን ኃላፊነት በተገቢው መንገድ የሚወጣበት አሠራር ለመዘርጋት ጥረቶች መደረጉን ለቋሚ ኮሚቴ አባላት ማብራሪያ ሠጥተዋል፡፡

ኃላፊው በተጨማሪም በተቋሙ ከዚህ በፊት በርካታ ችግሮች የሚታይ እንደነበርና ከፖለቲካ ወገንተኝነት ጋር በተያያዘ ሰፊ ችግሮች ይስተዋል እንደነበር  አንስተዋል፡፡

ተቋሙ በባለፉት የአገሪቱ ሥርዓቶች የመጣበት የአሠራርና የአደረጃጀት ዕድገት ዳራዎችን በተመለከተ ሽግግር እንዳልነበረውና ሰፊ ክፍተቶች እንዳሉበት ተገልጿል፡፡   

መሥሪያ ቤቱ ወቅቱ የሚፈልገው የሠለጠነ የሰው ኃይልና የቴክኖሎጂ እጥረቶች እንዳሉበት የገለጹት ጀነራል አደም የሚታዩ ክፍተቶችን ለማሟላት እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ 

"መረጃን እንለቃለን ታምነን እናገለግላለን" በሚል መሪ ቃል ተቋሙ በአዲስ አደረጃጀት ወደ ስራ የሚገባ እንደሆነና ይህም ተቋሙ በህዝብ የሚፈራ ሳይሆን ህዝብም እንደተቋም የራሱን አድርጎ በማሰብ የተቋሙን አሠራሮች በመደገፍና ማንኛውም ግለሰብ ከተቋሙ ጋር በሚኖረው ግንኙነት ግልፅ የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር ታሳቢ የሚያደርግ አሠራራ እንደሚዘረጋም  አመልክተዋል፡፡

በቅርብ ጊዜ  የተለያዩ  የአገር አቀፍ  ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች  የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ተቋሙን  አሠራር በተመለከተ  በተቋሙ በአካል  በመገኘት  ጉብኝት ማድረጋቸው  ይታወሳል ።