በምዕራብ ኦሮሚያ የፀጥታ ችግር ታይቶባቸው የነበሩ አካባቢዎች ወደ ሰላምና መረጋጋት እየተመለሱ ነው

በምዕራብ ኦሮሚያ የፀጥታ ችግር ታይቶባቸው የነበሩ አካባቢዎች ወደ ቀደመ ሰላማዊ የእለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው እየተመለሱ መሆኑን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

በምዕራብ ኦሮሚያ ባለፉት ወራት የሰዎችን ህይወት የቀጠፉ፣ የአካል እና ንብረት ጉዳት ያደረሱ ግጭቶች በተለይም በቄለም ወለጋ እና ምዕራብ ወለጋ በተደጋጋሚ ተከስተው አሳሳቢ ችግር ተፈጥሮ ነበር።

በምዕራብ ጉጂ፣ ምስራቅ ጉጂ፣ ሆሩ ጉድሩ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ኢሉ አባቦራ እና በደሌ በከፊል መሰል ችግሮች ታይተዋል።

አሁን ላይ መሻሻሎች እያታዩና የፀጥታ ችግር ታይቶባቸው የነበሩ አብዛኛዎቹ ከተሞችም ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴያቸው እየተመለሱ መሆኑን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀኔራል አለማየሁ እጅጉ ተናግረዋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ በፀጥታ ችግር ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶችና የጤና ተቋማት እንዲሁም መንገዶች ተዘግተው ነበር።

የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ሰላም ለማስፈን ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ ግን ተዘግተው የነበሩ የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት እየተከፈቱ መሆኑንም ነው ኮሚሽነር ጀኔራል አለማየሁ የተናገሩት።

ይሁን እንጅ ችግሩ አሁንም ሙሉ በሙሉ አለመፈታቱንና በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈፀሙ ትንኮሳዎች መኖራቸውንም አንስተዋል፤ በዚህ ሳቢያም የማህበራዊ አገልግሎት የተቋረጠባቸው አካባቢዎች እንዳሉ በመጥቀስ።

ጉዳዩ አሳሳቢ ነው ተብሎ ባይጠቀስም ከምዕራብ ወለጋ እና ቄለም ወለጋ ራቅ ብለው ድንበር ላይ የሚገኙ ቀበሌዎች እና ወረዳዎች መሻሻል ቢያሳዩም በተሟላ ሁኔታ አገልግሎት የማያገኙ ሥፍራዎች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የፀጥታ ችግር ባስተናገዱ አካባቢዎች የወደሙትን ቤቶች እና መስሪያ ቤቶች መልሶ የማደስ እና የፈረሱ የመንግስት መዋቅሮችን በድጋሚ የማደራጀት ስራ እየተሰራ ይገኛልም ነው ያሉት።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ህይወት በማጥፋት፣ ቤቶችን በማቃጠል፣ ባንኮችን በመዝረፍ እና መንገዶችን በመዝጋት የተጠረጠሩ አካላትን በቁጥጥር ስር እያዋለ መሆኑንም ገልጸዋል።

ፖሊስ ዜጎች ወደተረጋጋ ህይወት እንዲመለሱ እና ወጥቶ የመግባት ደህንነታቸው እንዲረጋገጥ እየሰራ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፥ ወንጀል ፈፃሚዎችን ለህግ በማቅረብ የህግ የበላይነት እንዲሰፍንም ሰፊ ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

ህብረተሰቡም የአካባቢውን ሰላም እና ፀጥታ ለማስጠበቅ እያደረገ ለሚገኘው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው፥ በቀጣይም የፀጥታ ሀይሎችን የመደገፍ እና ተጠርጣሪዎችን የማጋለጥ ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።(ኤፍቢሲ)