የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ በዛሬው ዕለት አዲስ አበባ ገብተዋል

የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ በዛሬው እለት በአፍረካ ህብረት ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ገብተዋል።

የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር የሆኑት የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ በዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ትኩረቱን ባደረገው ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ገብተዋል።

ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ  ሲደርሱ የኢፌዴሪ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ አቀባበል አድርገዋል።

የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች የሚሳተፉበት በዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የሚያተኩረው ጉባኤ በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

ጉባኤው በዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ በተፈጠረው ፓለቲካዊ አለመረጋጋት ዙሪያ ይመክራል ተብሎም ይጠበቃል።

የደቡብ አፍሪካ ልማት ማህበረሰብ አባል ሀገራት አዘጋጅነት የሚካሄደው ጉባኤም ሌሎችን አለም አቀፍ እና አህጉራዊ ድርጅቶች ይሳተፉበታል ተብሏል።

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳን ጨምሮ የተለያዩ አፍሪካ ሀገራት ይሳተፋሉ ተብሎም ይጠበቃል።

በቅርቡ በዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የተቃዋሚ ፓርቲ እጩው ፌሊክ ቲሽሴክዲ ማሸነፋቸውን የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ።

በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ  የተካሄደው  ምርጫ ውጤት የማይቀበሉ ተወዳዳሪዎች  በፈጠሩት ችግር  ምክንያት በሀገሪቱ ግጭት መከሰቱና የሰው ህይወት ማለፉ ይታወቃል።