የሪፍቲቫሊ ዩኒቨርሲቲ ባለቤት አቶ ድንቁ ደያስ ከቤኒሻንጉልና ኦሮሚያ ክልል ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ አደረጉ

የሪፍቲቫሊ ዩኒቨርሲቲ ባለቤት አቶ ድንቁ ደያስ ከቤኒሻንጉልና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች  ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ አደረጉ፡፡

በቅርቡ ከቤኒሻንጉልና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች እንዲሁም ከቤኒሻንጉል ካማሽ ዞንና ሌሎች ወረዳዎች በተፈጠረ ግጭት ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡

አቶ ድንቁ በምስራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴና አካባቢው ለተጠለሉ ዜጎች በግምት 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር የሆነ የምግብና አልባሳት ነው ድጋፍ ያደረጉት ፡፡

ይህንኑ ድጋፍ የሪፍቲ ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ነቀምቴ ካምፓስ ዲን አቶ ወንድሙ ቀኖ እና የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን በተገኙበት ለምስራቅ ወለጋ ዞን አስተዳደር አስረክበዋል፡፡

የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ብርሀኑ በቀለ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ተፈናቃዮችን ወደ መኖሪያ ቀያቸው የመመለስ ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀዋል ። 

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን የተለያዩ ባለሀብቶች በተለይም የነቀምቴ ከተማና አካባቢ ነዋሪዎች ለተፈናቃዮች ያደረጉትን ድጋፍ አድንቀዋል። 

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልል መንግስትም ተፈናቃዮች በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስ  ከጎናቸው እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል፡፡

በቅርቡ የሪፍቲ ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ነቀምቴ ካምፓስ ሠራተኞችም ከቤኒሻንጉል ለተፈናቀሉ ዜጎች ተመሳሳይ ድጋፍ ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡