ሀገራችን ቀደምት የእኩልነት፣ የነጻነትና የሰላም መገኛ እንደነበረች አልነጃሺ መስጂድ ምስክር ነው-ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

ሀገራችን ቀደምት የዜጎች የእኩልነት፣ የነጻነትና የሰላም መገኛ እንደነበረች ከአልነጃሺ መስጂድ መማር ይቻላል ሲሉ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳደር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ገለጹ።

ምክትል ርዕሰ-መስተዳደሩ በትግራይ ምስራቃዊ ዞን ክልተአውላሎ ወረዳ የሚገኘውን የአልነጃሺ መስጊድን ከተለያዩ ሃገራት ከመጡ የእምነቱ አባቶች ጋር ጎብኝተዋል።

ኢትዮጵያ ለዜጎቿ ይቅርና ለሌሎች የምትሆን ሃገር እንደነበረች፣ እምነትና አስተሳሰብ ለግል ሆኖ በጋራ የተገነባች ሃገር መሆኗን ከነጃሺ መስጊድ ማረጋገጥ እንደሚቻል ተናግረዋል።

“ቱሪዝም ማለት ህንጻ ብቻ አይደለም” ያሉት ምክትል ርዕሰ-መስተዳደሩ ታሪክና እውነታን ማሳወቅ ተገቢ መሆኑን በመግለጽ “በአልነጃሺ ያለውን ያልተገለጸ ታሪክ በማስረዳት የቱሪዝም መስህብ ለማድረግ እንሰራለን” ብለዋል።

የኢትዮጰያ እስልምና ጉዳዮች ፕሬዝዳንት ሼህ መሃመድ አሚን ጀማል በበኩላቸው ነብዩ መሀመድ ተከታዮቻቸውን ወደ ሀበሻ ምድር ሲልኩ የሰላም ሀገር መሆኑን በመገንዘብ ነው ብለዋል፡፡

“በዚህም አልነጃሺ መስጂድን ስናነሳ የሀይማኖት ነፃነት የተስፋፋበትና የዴሞክራሲ ተምሳሌት በመሆኑ ለአለም ህዝብ ማስተዋወቅ ይገባናል” ብለዋል።

የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ፕሬዝዳንት ሼህ አደም አብዱልቃድር “ስለእስልምና ሃይማኖት ስናወራ ስለታሪካችን ነው የምናወራው፣ ስለታሪካችን ስናወራ ደግሞ ስለአልነጃሺ ነው” ብለዋል።

“አልነጃሺ የሃይማኖት መቻቻል የሚያስተምር በመሆኑ ልጆቻችንን ስለዚህ ጉዳይ ማስተማር አለብን” ሲሉም ሼህ አደም ገልጸዋል፡፡

በዕለቱ ከ20 ዓመታት መለያየት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጡ የኤርትራ የእስልምና አባቶችን ጨምሮ የሱዳንና የኢትዮጵያ የእምነቱ አባቶች ተገኝተዋል። (ምንጭ፡-ኢዜአ)