ሰላም ፍጥረታትን በአንድ ቋንቋ ማስተሳሰር የሚያስችል ታላቅ ኃይል ነው – የሰላም ሚኒስቴር

ሰላም የሰው ልጆችን ብቻ ሳይሆን ፍጥረታትን በአንድ ቋንቋ ማስተሳሰር የሚያስችል ታላቅ ኃይል ነው ሲሉ የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን ገለጹ፡፡

የሰላም ሚኒስቴር ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋር በመሆን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሰላም በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውይይት አካሂደዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ወ/ሮ አልማዝ መኮንን የሰላም ሚኒስቴር ሲቋቋም በአገራችን ብሎም በቀጠናው ሰላምን የማረጋገጥ ተልዕኮ እና የህግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊነት ተሰጥቶት የተመሰረተ መስሪያ ቤት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአገራችን በአንድ አንድ ዩኒቨርስቲዎች ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ ግጭቶች እየተነሱ ተማሪዎች ሲቸገሩ ይሰተዋላል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታ ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች እውቀትንና ክህሎትን የጋራ ዓላማ አድርገው የተለያዩ ባህል፣ ቋንቋና ኃይማኖት ያላቸው ኢትዮጵያዊያን በአንድ ላይ የሚገናኙበት የብዝሃነት አውራ መገለጫዎች ትንሿ ኢትዮጵያ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የዕውቀት መፍለቂያ በሆኑ ተቋማት የምትገኙ የዛሬ ተማሪዎች ብዝሃነታችሁ ውበታችሁ፣ ብዝሃነታችሁ የፈጠራና የብልፅግና ምንጭ መሆኑን አውቃችሁ በሰላም ጉዳይ እንድ ላይ ሁናችሁ በመቆም ለአገር ግንባታና ሰላም ዘብ መቆም እንዳለባቸዉ ሚኒስትር ዴኤታዋ ለተማሪዎች ምክር አስተላልፈዋል፡፡

ሚኒስቴር ዴኤታዋ ወ/ሮ አልማዝ መኮንን ለመምህራን ባስተላለፉት መልዕክት በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ትርክቶችን ሙህራዊ አቅማችሁንና ሙያዊ ስነምግባራችሁን መሰረት አድርጋችሁ እውነታውን ለተማሪዎቻችሁና ለአጠቃላይ ማህበረሰቡ ማሳወቅና ማስገንዘብ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ የኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው ሰላምና ልማት ቀጥተኛ ተዛማጅነት ያላቸው ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው፤ ያለ ሰላም ቀጣይነት ያለው ልማት ዕውን ማድረግም ሆነ የዜጎችን ደህንነት ማረጋገጥ ፈፅሞ የማይታሰብ መሆኑን ተናግረው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቱ ምክኒያታዊና አለማቀፋዊ አስተሳሰብ ያለው ዜጋ ለማፍራት እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በኮንፈረንሱ ላይም በተለያዩ የዘርፉ ምሁራን ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎችም በቀረቡ ጥናታዊ ፅሁፎች ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተው ተወያይተዋል፡፡

በሰላም ኮንፈረንሱ የሰላም ሚኒስቴር አመራሮችና ባለሙያዎች፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራንና ተማሪዎች፣ ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የተወጣጡ ተማሪዎችና መምህራን፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላትና ሌሎች ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡ (ምንጭ፡-የሰላም ሚኒስቴር)